ራሳቸውን መጥቀም እንዲችሉ አስተምሯቸው
1 ይሖዋ ሰዎች ሁሉ ራሳቸውን መጥቀም እንዲችሉ ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17 NW) እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። የእርሱ ልባዊ ምኞት የሰው ልጆች ጥፋት ከሚያስከትልባቸው መንገድ ርቀው የእርሱን ትእዛዛት በመከተል አርኪ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው። ሕይወታችንን በአምላክ መንገድ ስንመራ ራሳችንን እየጠቀምን ነው። (መዝ. 34:8) ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ እንዴት ማስተማር እንችላለን?
2 ሰዎች የሚፈልጉት ምንድን ነው? በምትኖርበት አካባቢ ያሉትን ሰዎች የሚያሳስባቸው ነገር ምንድን ነው? መኖሪያ ቤታቸው አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘቱ፣ ትዳራቸው የጸና መሆኑ፣ የልጆቻቸው የወደፊት ሕይወትና የመሳሰሉት ጉዳዮች አይደሉም? ችግር ሲያጋጥማቸው እርዳታ ለማግኘት ዞር የሚሉት ወዴት ነው? በራሳቸው አስተሳሰብ፣ በራስ አገዝ ፕሮግራሞች ወይም ሌሎች በሚሰጧቸው ሐሳብ ይመሩ ይሆናል። እንዲህ በማድረጋቸውም ብዙዎች ራሳቸውን መጥቀም የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ በሚነገሯቸው ተግባራዊና ወጥ ያልሆኑ ሐሳቦች የተነሳ ግራ ይጋባሉ። የአምላክ ቃል የሚሰጠን መመሪያ እጅግ የተሻለ መሆኑን አሳማኝ ማስረጃ ልናቀርብላቸው ይገባል። (መዝ. 119:98) ይህን ማድረግ የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና በውስጡ ያለውን መመሪያ በሥራ ለማዋል ጥረት ካደረጉ አሁንም እንኳ ሕይወታቸውን እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ በማሳየት ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17
3 የተሻለ የቤተሰብ ሕይወት፦ በኤፌሶን 5:22–6:4 ላይ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር የቤተሰብ ችግሮችን ለመፍታት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የሚያስተውሉት ጥቂት ሰዎች ናቸው። ለአሥር ዓመታት ያህል በጋብቻ ተሳስረው ከኖሩ በኋላ ለመለያየት የወሰኑ የአንድ ባልና ሚስት ሁኔታ ይህን ያሳያል። ይሁን እንጂ ሚስትየዋ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረችና ትዳርን በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተማረች። ባልየው ብዙም ሳይቆይ ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ በማዋል ያደረገቻቸውን ለውጦች በማስተዋሉ እርሱም ጥናቱ ላይ መገኘት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ “አሁን እውነተኛ ደስታ ለሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት መሠረት የሆነውን ነገር አግኝተናል” ሲል ተናግሯል።
4 ትክክለኛ የሕይወት ዓላማ፦ የዕፅ ሱሰኛ የሆነ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችን እርዳታ ለማግኘት በሞከረበት ወቅት ይሖዋ በግል ስለ እርሱ እንደሚያስብለት አስረዱት። እንዲህ ሲል ገለጸ:- ‘ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያወጣው ዓላማ እንዳለና በፊቱ ሞገስ ላገኙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዳዘጋጀላቸው አወቅሁ። ይህን በማወቄ የተሰማኝን ደስታ ይህ ነው ብዬ ልገልጽላችሁ አልችልም። በዛሬው ጊዜ ጥሩ ጤና፣ የአእምሮ ሰላምና ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና አግኝቻለሁ።’
5 ማንኛውም ሰው በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው ተግባራዊ እርዳታ ጥቅም ማግኘት ይችላል። ቃሉን መመሪያችን አድርገን በመጠቀም የይሖዋ መንገድ ዓለም ከሚከተለው መንገድ እጅግ የላቀ መሆኑን አረጋግጠናል። (መዝ. 116:12) ሌሎች ራሳቸውን መጥቀም እንዲማሩ ይህን መልእክት የማድረስ መብት አግኝተናል። እንዲህ ስናደርግ በርካታ ግሩም ውጤቶች እናገኛለን።