ልትረዷቸው ትችሉ ይሆን?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ የጉባኤ አባላት “እርስ በራሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ” መክሯል። (1 ቆሮ. 12:25) ስለሆነም እርስ በርሳችን በግል አሳቢነት ማሳየትና የሚያስፈልግ ሲሆን ፍቅራዊ ዕርዳታ ለመስጠት ፈቃደኞች መሆን አለብን። ለምሳሌ ያህል በመካከላችን ያሉ አንዳንድ መንፈሳዊ እህቶች ልጆቻቸውን በእውነት ውስጥ የሚያሳድጉት ብቻቸውን ነው። እነዚህ እህቶች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ስልጠና የመስጠቱን ሙሉ ኃላፊነት ተሸክመዋል። በእርግጥም ‘አስፈላጊ በሆነበት አቅጣጫ ሁሉ’ የደግነት ማበረታቻና ተግባራዊ እገዛ ልንሰጣቸው ይገባል። (ሮሜ 12:13ሀ) ልትረዷቸው ትችሉ ይሆን?
2 መርዳት የምትችሉባቸው መንገዶች፦ ወደ ጉባኤና ትልልቅ ስብሰባዎች ለመሄድ የግድ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ከሆነ አብረዋችሁ በመኪና እንዲሄዱ ብታደርጉ ለዚያ ቤተሰብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሊቆጥብለት ይችላል። በስብሰባ ላይ የአንዲትን እናት ትንንሽ ልጆች መንከባከብ እሷ ከፕሮግራሙ ይበልጥ ጥቅም እንድታገኝ ያስችላት ይሆናል። በተመሳሳይም ልጆቿን ይዛ አገልግሎት በምትወጣበት ጊዜ መርዳት ለእሷ እፎይታን ሊሰጣት ይችላል። እነሱን ጓደኛ በማድረግ ለልጆቹ ልባዊ ትኩረት መስጠት በወጣቶቻችን ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ነጠላ ወላጆች ያሏቸውን ቤተሰቦች አልፎ አልፎ በቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ከፍተኛ መንፈሳዊ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል።
3 አስተዋዮች ሁኑ፦ እርዳታችን እንደማያስፈልጋቸው የሚሰማቸውን ግን እንዳናስገድዳቸው ጠንቃቆች መሆን አለብን። የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በምንሰጥበትም ጊዜ እንኳን በቤተሰብ ጉዳዮቻቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት አይኖርብንም። እርግጥ እርዳታ የሚያስፈልጋትን አንዲት እህት የሚያግዟት እህቶችና ባልና ሚስቶች ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል።
4 ሁሉም ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ‘እንግዶችን ለመቀበል እንዲተጉ’ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 12:13ለ) ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የእርዳታ እጃችንን መዘርጋታችን በመካከላችን ያለውን የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ከምናሳይባቸው ብዙ መንገዶች አንዱ ነው።—ዮሐ. 13:35