የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ
1 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በአገልግሎታቸው የይሖዋን በረከት ማግኘታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። (ማቴ. 9:37, 38) ልባዊ ከሆነ ምልጃና ልመና ጋር የምናቀርበው የውዳሴና የምስጋና ጸሎት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እርዳታ ላይ እንደምንታመን ያሳያል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ቅዱሳን ጽሑፎች “በጸሎትና በልመናም ሁሉ” እንድንጸና አጥብቀው ይመክሩናል፤ ይህ ደግሞ አገልግሎታችንንም አስመልክተን ለምናቀርበው ጸሎት ይሠራል።—ኤፌ. 6:18
2 ይሖዋን አቻ ለሌላቸው ባሕርያቱና ሥራዎቹ በጸሎት እናወድሰዋለን። የምንሰብከውንም የምሥራች የሰጠን እርሱ ስለሆነ እናወድሰዋለን። የአገልግሎታችን ስኬታማነት የተመካው በእርሱ ላይ ስለሆነ ልናወድሰው ይገባል።—መዝ. 127:1
3 የምናቀርበው የምስጋና ጸሎት ይሖዋ ፈቃዱንና ዓላማውን አስመልክቶ ለሰጠን ማስተዋል ያለንን አድናቆት ይገልጻል። የመንግሥቱን እውነት ለሌሎች ማካፈል ልዩ መብት አይደለምን? በአገልግሎቱ ለምናከናውነው ነገር ሁሉ ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—መዝ. 107:8፤ ኤፌ. 5:20
4 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የምናቀርብላቸውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች ለማግኘትና እውነት ልባቸውን እንዲነካው ለማድረግ እንችል ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳን መጠየቃችን ተገቢ ነው። እንደዚህ ያሉ ልመናዎች ማቅረባችን በአገልግሎቱ የምናከናውነው ሥራ ፍሬያማነት የተመካው በአምላክ ላይ መሆኑን አምነን እንደምንቀበል ያሳያል።—1 ቆሮ. 3:5-7
5 አንዲት እህት የመጽሔት ደንበኛዋ የምትወስዳቸውን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች እንደማታነባቸው ተሰማት። እነዚህ ውድ መጽሔቶች እንዲባክኑ ስላልፈለገች ሴትየዋ ወስዳ ሳታነባቸው ከሚቀሩ አልፈልግም እንድትላት ይሖዋን ለመነችው። እህት የሚቀጥለው ጊዜ ስትሄድ የዚህች ሴት ባል እንዲህ አላት:- “እነዚህን መጽሔቶች ዘወትር ስለምታመጪልን አመሰግንሻለሁ። እኔ እያነበብኳቸው ነው ደግሞም እወዳቸዋለሁ።”
6 የሰዎችን ግዴለሽነትና ፌዝ በመቋቋምና ማንኛውንም ሰውን የመፍራት ችግር በማሸነፍ ለሌሎች በድፍረት መመሥከራችንን መቀጠል እንድንችል ይረዳን ዘንድ ይሖዋን በትህትና ከልብ በመነጨ ስሜት ልንለምነው እንችላለን። (ሥራ 4:31 የ1980 ትርጉም) “በጸሎትና በልመናም ሁሉ” በመጽናት ቅዱስ አገልግሎታችንን በታዛዥነት የምንፈጽም ከሆነ ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ዮሐ. 3:22