ለመንግሥት አዳራሽ የግንባታ ሥራ ድጋፍ መስጠት ትችል ይሆን?
1 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ነበሩ። ድፍረት የተሞላበት ስብከታቸው እውነተኛው አምልኮ ወደ እስያ፣ አፍሪካና አውሮፓ እንዲዳረስ ያስቻለ ሲሆን ጉባኤዎች ባሳዩት እድገትም ተደስተው ነበር። (ሥራ 16:5) በዚህ የፍጻሜ ዘመን እውነተኛው አምልኮ በዓለም ዙሪያ ተስፋፍቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ ከ300,000 ሰዎች በላይ ይጠመቃሉ! ይህ ፈጣን እድገት ብዙ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።
2 ይህን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በአንገብጋቢ ሁኔታ የመንግሥት አዳራሽ ለሚያስፈልጋቸው ሆኖም ባለባቸው የኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ አቅማቸው ውስን ለሆነ ጉባኤዎች ከማኅበሩ የመንግሥት አዳራሽ ገንዘብ ብድር እንዲሰጥ የአስተዳደር አካሉ ዝግጅት አድርጓል። በመሆኑም በዚህ የገንዘብ እርዳታ አማካኝነት አስፈላጊ በሆነበት ቦታ መሬት እየተገዛ ሲሆን ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ልከኛ ሆኖም ማራኪ የመንግሥት አዳራሾች በመገንባት ላይ ናቸው። የእኛን ጨምሮ በበርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዴስክ እየተቋቋመ ነው። ይህ ዝግጅት ብዙ መሻሻል እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ጊዜም ሆነ ገንዘብ የሚቆጥቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ፕላኖችና የግንባታ ዘዴዎች በመነደፍ ላይ ናቸው። ለሥራው አመራር የሚሰጡ ልምድ ያላቸው ወንድሞች ለማግኘትና በግንባታ ሥራ አደረጃጀትና በአንዳንድ ሙያዎች የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ለማሠልጠን ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።
3 ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች መገንባት እንዲቻል የዚህ እርዳታ ተጠቃሚ የሆኑ ጉባኤዎች የተበደሩትን ገንዘብ ለመተካት ቋሚ የሆነ ወርኃዊ አስተዋጽኦ እንዲልኩ እናበረታታቸዋለን። እንዲሁም ግቢውና ሕንፃው እውነተኛውን አምልኮ የሚያስከብር ሆኖ እንዲቀጥልና ረጅም ዕድሜ እንዲኖረው ጥሩ የዕደሳ ፕሮግራም ለመከተልም ይስማማሉ። እንዲህ በማድረግ አላስፈላጊ ወጪዎችን ማስቀረት ይቻላል።
4 ይህ ፕሮግራም ስኬታማ እንዲሆን ፈቃደኛ ሠራተኞች የግድ ያስፈልጋሉ። በበርካታ አገሮች የሚገኙ በሙያው የተካኑ ወንድሞች የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ የግንባታ ሠራተኞች በመሆን እርዳታ ለማበርከት ሲሉ ለወራት አንዳንዴም ለዓመታት ከሥራቸው ሊያገኙ የሚችሉትን ገቢ ሠውተዋል። በርከት ያሉ ሌሎች ደግሞ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ላይ በሥራው ለመሳተፍ ራሳቸውን ነፃ አድርገዋል አሊያም ለቀናት ወይም ለሳምንታት እረፍት ወስደዋል። አንዳንዶች ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን በነፃ በመለገስ በየቀኑ ለተወሰነ ሰዓት እርዳታ ለማበርከት መጥተዋል። የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማራመድ ያላቸው ፍላጎት የስብከቱን ሥራ ብቻ ሳይሆን የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ግንባታ የሚያካትተውን ይህን የእውነተኛ አምልኮ ዘርፍ ለመደገፍም አነሳስቷቸዋል። (መዝ. 110:3 NW) በቅርቡ አብዛኞቻችን እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እናገኛለን። በአገራችንም ብዙዎች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንደሚያሳዩ ትምክህት አለን። አንተም ከእነርሱ መካከል ትገኝ ይሆን?