የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 3—ዘሌዋውያን
ጸሐፊው:- ሙሴ
የተጻፈበት ቦታ:- ምድረ በዳ
ተጽፎ ያለቀው:- 1512 ከዘአበ
የሚሸፍነው ጊዜ:- 1 ወር (1512 ከዘአበ)
ሦስተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ዘሌዋውያን የሚለውን በስፋት የሚጠራበትን ስም ያገኘው የላቲኑ ቩልጌት ሌዊቲከን ከሚለው የግሪክ ሰፕቱጀንት ስያሜ በመነሣት ከሰጠው “ሌቪቲከስ” ከሚለው ትርጉም ነው። ምንም እንኳን መጽሐፉ ሌዋውያንን በሚመለከት የሚናገረው ነገር ጥቂት ቢሆንም (25:32, 33 ላይ) በአብዛኛው ከሌዊ ነገድ ተመርጠው ክህነታዊ አገልግሎት የሚሰጡት ሌዋውያን ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር የተያያዙ ደንቦችን የያዘና “ካህኑ . . . ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፣ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል” በሚለው መሠረት ካህናቱ ለሕዝቡ የሚያስተምሩትን ሕግጋት የያዘ በመሆኑ በዚህ ስም መጠራቱ ተገቢ ነው። (ሚል. 2:7) በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ መጽሐፉ ስሙን ያገኘው በመጽሐፉ መክፈቻ ላይ ከሚገኘው ዋይዪቅራ ከሚለው ቃል ሲሆን ይህም ቃል በቃል ሲተረጎም ‘ጠራው’ የሚል ትርጉም አለው። በኋለኛው ዘመን በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ መጽሐፉ የካህናቱ ሕግና የመሥዋዕት ሕግ ተብሎም ይጠራ ነበር።—ዘሌ. 1:1፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።
2 የዘሌዋውያንን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም። የመጽሐፉ መዝጊያ “እግዚአብሔር . . . ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው” ይላል። (27:34) ዘሌዋውያን 26:46 ላይም ተመሳሳይ ዓረፍተ ነገር ይገኛል። ሙሴ ዘፍጥረትንና ዘጸአትን እንደጻፈ ማረጋገጫ የሚሆኑት ከዚህ ቀደም የቀረቡት ማስረጃዎች የዘሌዋውያንንም መጽሐፍ የጻፈው እርሱ ለመሆኑ ማስረጃ ይሆናሉ። ምክንያቱም ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በመጀመሪያ አንድ ጥቅልል ነበሩ። ከዚህም በላይ የሌዋውያን መጽሐፍ ከርሱ በፊት ከነበሩት መጻሕፍት ጋር “ም” በሚለው መስተፃምር የተያያዘ ነው። ከሁሉም የላቀው ጠንካራ ማስረጃ ግን ኢየሱስ ክርስቶስና ሌሎች በመንፈስ ቅዱስ የተነዱ የይሖዋ አገልጋዮች ከዘሌዋውያን መጽሐፍ ሕግጋትንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተደጋጋሚ መጥቀሳቸውና ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ ማመልከታቸው ነው።—ዘሌ. 23:34, 40-43—ነህ. 8:14, 15፤ ዘሌ. 14:1-32—ማቴ. 8:2-4፤ ዘሌ. 12:2—ሉቃስ 2:22፤ ዘሌ. 12:3—ዮሐ. 7:22፤ ዘሌ. 18:5—ሮሜ 10:5
3 ዘሌዋውያን የሚሸፍነው ምን ያህል ጊዜ ነው? የዘጸአት መጽሐፍ የማደሪያው ድንኳን “በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን” መተከሉን በመግለጽ ታሪኩን ይደመድማል። የዘኁልቅ መጽሐፍ (የዘሌዋውያንን ታሪክ ተከትሎ) “በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፣ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት” ይሖዋ ሙሴን እንዳነጋገረው በመግለጽ ታሪኩን ይጀምራል። ሕግጋትንና ደንቦችን በብዛት አካቶ የያዘው የዘሌዋውያን መጽሐፍ በውስጡ የያዛቸው ጥቂት ታሪኮች በአንድ የጨረቃ ወር ጊዜ ውስጥ ተከናውነው ሊያልቁ የሚችሉ በመሆናቸው የዘኁልቁ መጽሐፍ ወዲያው ተከትሎ ይመጣል።—ዘጸ. 40:17፤ ዘኁ. 1:1፤ ዘሌ. 8:1-10:7፤ 24:10-23
4 ሙሴ ዘሌዋውያንን የጻፈው መቼ ነው? እያንዳንዱ ክንውን እንደተፈጸመ ወይም መመሪያዎቹን ከአምላክ እንደተቀበለ ወዲያው ይጽፋቸው ነበር ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። እስራኤላውያን አማሌቃውያንን ወግተው ካሸነፉ በኋላ ሙሴ ታሪኩን ወዲያው እንዲጽፍ አምላክ ማዘዙ የዚህን አባባል እውነተኝነት የሚያጠነክር ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ አንዳንድ ጉዳዮች መጽሐፉ ቀደም ብሎ እንደተጻፈ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን ለምግብነት ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጓቸውን እንስሳት ወደ መገናኛው ድንኳን አምጥተው እንዲያርዷቸው ታዝዘው ነበር። ይህ ትእዛዝ ሊሰጥና ሊመዘገብ የሚችለው የክህነት አገልግሎት ከተቋቋመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መሆን አለበት። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት የሚመሩባቸው በርካታ መመሪያዎች ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሙሴ የዘሌዋውያንን መጽሐፍ በ1512 ከዘአበ እንደጻፈው የሚያመለክቱ ናቸው።—ዘጸ. 17:14፤ ዘሌ. 17:3, 4፤ 26:46
5 ዘሌዋውያን ለምን ተጻፈ? ይሖዋ ለእርሱ አገልግሎት የተለየ ቅዱስና ንጹሕ ሕዝብ እንዲኖረው ዓላማ ነበረው። ከአቤል ጊዜ ጀምሮ የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ መሥዋዕት ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ሌሎች መሥዋዕቶችን ጨምሮ ለኃጢአት የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን በሚመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ የሆነ መመሪያ የሰጠው ለእስራኤል ብሔር ነበር። በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር የቀረቡት እነዚህ መመሪያዎች እስራኤላውያን ኃጢአት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነና ይሖዋን ምን ያህል ሊያሳዝኑት እንደሚችሉ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። እነዚህ በሕጉ ውስጥ የሚገኙ መመሪያዎች አይሁዳውያንን ወደ ክርስቶስ ለማድረስ እንደ አስተማሪ ሆነው አገልግለዋል። አዳኝ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል እንዲሁም ሕዝቡ ከተቀረው ዓለም የተለዩ ሆነው እንዲኖሩ ረድተዋቸዋል። በተለይ ስለ መንጻት ሥነ ሥርዓት የሚናገሩት የአምላክ ሕጎች ሕዝቡን ከተቀረው ዓለም የተለዩ ሆነው እንዲኖሩ ረድተዋቸዋል።—ዘሌ. 11:44፤ ገላ. 3:19-25 NW
6 የእስራኤል ሕዝብ ከዚያ ቀደም አይቶት ወደማያውቀው ምድር እየተጓዘ ያለ አዲስ ብሔር ስለነበር ተገቢውን መመሪያ ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ከግብፅ ነፃ ከወጡ አንድ ዓመት እንኳ ያልሞላቸው በመሆኑ የግብፃውያን አኗኗርና ሃይማኖታዊ ልማዶች ገና ከአእምሯቸው አልጠፉም ነበር። በወንድምና በእህት መካከል ጋብቻ መመሥረት በግብፅ የተለመደ ነገር ነበር። ለብዙ አማልክት ክብር ሲባል የሐሰት አምልኮ ይከናወን ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አማልክት እንስሳት ነበሩ። አሁን ደግሞ ይህ ትልቅ ጉባኤ አኗኗሩና ሃይማኖታዊ ልማዶቹ እጅግ ወደ ከፋው ወደ ከነዓን ምድር እያመራ ነው። ነገር ግን የእስራኤልን ሰፈር አንድ ጊዜ መለስ ብለን እንቃኝ። በጉባኤው መካከል ግብፃዊ ወላጅ የነበራቸውና በግብፃውያን ወግ፣ ትምህርት፣ ሃይማኖትና ብሔራዊ ስሜት ያደጉ ንጹሕ ግብፃውያን ወይም ከግብፃውያን ጋር የተዳቀሉ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ ነበሩ። አብዛኞቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተወለዱበት አገር ይካሄዱ በነበሩት አስጸያፊ ልማዶች ይካፈሉ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ወቅት ከይሖዋ ዝርዝር መመሪያ ማግኘታቸው ምንኛ የተገባ ነው!
7 የዘሌዋውያን መጽሐፍ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎችን ይዟል። እነዚህ ጥበብና ፍትሕ የተንጸባረቀባቸው ሕጎችና መመሪያዎች የሰው ሐሳብ ያፈለቃቸው ሊሆኑ አይችሉም። አመጋገብን፣ በሽታን፣ መገለልንና ሬሳን በተመለከተ ሊደረግ የሚገባውን ነገር አስመልክቶ የተሰጡት ደንቦች በዓለም ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ከዚያ በኋላ በነበሩት ብዙ ሺህ ዓመታት እንኳ ያልተረዷቸው እውነታዎች ነበሩ። ንጹሕ ስላልሆኑት እንስሳት የሚናገረው የአምላክ ሕግ በጉዞ ላይ የነበሩትን እስራኤላውያን ጠብቋቸዋል። በአሳማዎች ላይ ከሚታየው ትራይኪኖሲስ ከተባለ በሽታ፣ ከተወሰኑ የዓሣ ዝርያዎች ከሚመጣው ታይፎይድና ፓራታይፎይድ የተባሉ በሽታዎች እንዲሁም ከሞቱ እንስሳት ከሚመጣ በሽታ ጠብቋቸዋል። እነዚህ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሕጎች ሃይማኖታቸውንና አኗኗራቸውን በመምራት ሕዝቡ ቅዱስ ሆኖ እንዲኖርና ለተስፋይቱ ምድር እንዲበቃ አድርገዋል። የአይሁድ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ በተሻለ መንገድ ጤንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ያስቻለው ይሖዋ የሰጣቸው ደንብና ሥርዓት እንደሆነ ታሪክ ያረጋግጣል።
8 በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶችና ትንቢታዊ ጥላዎች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው መጽሐፉ በመንፈስ አነሳሽነት ለመጻፉ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣሉ። በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ አለመታዘዝ ሊያስከትል ስለሚችለው መዘዝ የተነገሩት ማስጠንቀቂያዎች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ቅዱሳን ጽሑፎችም ሆኑ ዓለማዊ ታሪኮች አረጋግጠዋል። ከሌሎቹ በተጨማሪ እናቶች በረሃብ ምክንያት የወለዷቸውን ልጆች እንደሚበሉ የተነገረው ትንቢት ይገኝበታል። ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ በጠፋችበት ወቅት ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ኤርምያስ አመልክቷል። እንዲሁም ጆሴፈስ በሌላ ወቅት ማለትም በ70 እዘአ ከተማዋ በድጋሚ በጠፋችበት ወቅት ይህ ሁኔታ መከሰቱን ጽፏል። ንስሐ ከገቡ ይሖዋ እንደሚያስባቸው የሚናገረው ትንቢታዊ የተስፋ ቃል በ537 ከዘአበ ከባቢሎን በተመለሱበት ወቅት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘሌ. 26:29, 41-45፤ ሰቆ. 2:20፤ 4:10፤ ዕዝራ 1:1-6) የዘሌዋውያን መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ማረጋገጫ የሚሆነው ሌላው ማስረጃ ደግሞ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መጽሐፉ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደሆነ በመቀበል ከዚሁ መጽሐፍ እየጠቀሱ መናገራቸው ነው። ሙሴ የመጽሐፉ ጸሐፊ መሆኑን ከሚያረጋግጡት ቀደም ሲል ከሰፈሩት ማስረጃዎች በተጨማሪ ማቴዎስ 5:38፤ 12:4፤ 2 ቆሮንቶስ 6:16ንና 1 ጴጥሮስ 1:16ን እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።
9 የዘሌዋውያን መጽሐፍ ተጀምሮ እስኪያልቅ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነት አጉልቶ ይገልጻል። ሕጎቹን የሰጠው ይሖዋ እንደሆነ 36 ለሚያክል ጊዜ ተገልጿል። ይሖዋ የሚለው ስም በእያንዳንዱ ምዕራፍ በአማካይ አሥር ጊዜ ያህል የሚገኝ ሲሆን “እኔ ይሖዋ ነኝ” በሚለው ማሳሰቢያ አማካኝነት ለአምላክ ቃል የመታዘዝ ጉዳይ በተደጋጋሚ ተገልጾላቸዋል። ቅድስና የሚለው ጭብጥ በመላው የዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህን ብቃት በመግለጽ ረገድ የዚህን ያህል በተደጋጋሚ የተገለጸበት ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም። ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ እስራኤላውያንም ቅዱሳን መሆን ነበረባቸው። የተወሰኑ ሰዎች፣ ቦታዎች፣ ዕቃዎችና አንዳንድ ወቅቶች ቅዱስ እንደሆኑ ተደርገው ተለይተው ነበር። ለምሳሌ ያህል የስርየት ቀንና የኢዩቤልዩ ዓመት በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ልዩ በዓል የሚከበርባቸው ወቅቶች እንዲሆኑ ተለይተው ነበር።
10 የዘሌዋውያን መጽሐፍ ቅድስናን ጎላ አድርጎ የሚገልጽ በመሆኑ ደም መፍሰሱ ማለትም ሕይወት መሥዋዕት መደረጉ ለኃጢአት ይቅርታ እንደሚያስገኝ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። ለመሥዋዕትነት የሚቀርቡት ንጹሕ የሆኑ የቤት እንስሳት ብቻ ነበሩ። አንዳንድ ኃጢአቶች መሥዋዕት ከማቅረብ በተጨማሪ መናዘዝን፣ መመለስንና ካሳ መክፈልን የሚጠይቁ ነበሩ። አንዳንድ ኃጢአቶች ደግሞ የሞት ቅጣት ያስበይኑ ነበር።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
28 የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆነው የዘሌዋውያን መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖችም ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ፍጥረታቱን ስለሚይዝበት መንገድ ያለንን ግንዛቤ ያጎለብትልናል። ለፍጥረታቱ የሚያደርገውን አያያዝ በቃል ኪዳኑ ሥር ለነበሩት እስራኤላውያን ካደረገው ነገር መመልከት ይቻላል። የዘሌዋውያን መጽሐፍ ሁልጊዜ የሚሠሩ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። እንዲሁም እምነት የሚያጠነክሩ በርካታ ትንቢታዊ አምሳያዎችንና ትንቢቶችን ይዟል። ብዙዎቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በድጋሚ የተገለጹ ሲሆን አንዳንዶቹም በቀጥታ ከዘሌዋውያን የተወሰዱ ናቸው። ሰባት ጎላ ያሉ ነጥቦች ከዚህ በታች ተብራርተዋል።
29 (1) የይሖዋ ሉዓላዊነት:- ይሖዋ ሕግ ሰጪ ሲሆን እኛም ፍጥረቶቹ እንደመሆናችን መጠን በእርሱ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን። ለእርሱ ፍርሃት እንዲያድርብን ማዘዙም የተገባ ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ልዑል እንደመሆኑ መጠን በጣዖት አምልኮም ይሁን በመናፍስት ሥራ ወይም በየትኛውም ዓይነት አጋንንታዊ ተግባር በመጠመድ የሚቀናቀኑትን ዝም ብሎ አያልፍም።—ዘሌ. 18:4፤ 25:17፤ 26:1፤ ማቴ. 10:28፤ ሥራ 4:24
30 (2) የይሖዋ ስም:- ስሙ በቅድስና መያዝ ያለበት ሲሆን በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን በስሙ ላይ ነቀፋ እንዳናመጣ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ዘሌ. 22:32፤ 24:10-16፤ ማቴ. 6:9
31 (3) የይሖዋ ቅድስና:- ይሖዋ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡም ቅዱሳን ማለትም ለአንድ የተለየ ዓላማ ወይም ለእርሱ አገልግሎት የተለዩ መሆን አለባቸው። ይህም በዙሪያችን ካለው ከአምላክ የራቀ ዓለም የተለዩ ሆኖ መኖርን ይጨምራል።—ዘሌ. 11:44፤ 20:26፤ ያዕ. 1:27፤ 1 ጴጥ. 1:15, 16
32 (4) የኃጢአት አስከፊነት:- አንድ ነገር ኃጢአት መሆኑንና አለመሆኑን ሊወስን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው፤ እኛም ኃጢአት እንዳንሠራ መጠንቀቅ አለብን። ኃጢአትን ለማስተሰረይ ሁልጊዜ መሥዋዕት መቅረብ ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ እንድንናዘዝ፣ ንሥሐ እንድንገባና የተቻለውን ያህል ማካካሻ እንድናቀርብ ይጠይቅብናል። አንዳንድ የኃጢአት ዓይነቶች ይቅርታ የማይደረግላቸው ናቸው።—ዘሌ. 4:2፤ 5:5፤ 20:2, 10፤ 1 ዮሐ. 1:9፤ ዕብ. 10:26-29
33 (5) የደም ቅድስና:- ደም ቅዱስ ስለሆነ በምንም መልኩ ወደ ሰውነታችን እንዲገባ ማድረግ የለብንም። ደምን መጠቀም የሚቻለው ኃጢአትን ለማስተሰረይ ብቻ ነው።—ዘሌ. 17:10-14፤ ሥራ 15:29፤ ዕብ. 9:22
34 (6) አንጻራዊ ጥፋተኝነትና ቅጣት:- ሁሉም ዓይነት ኃጢአቶችና ኃጢአተኞች በእኩል ዓይን አይታዩም። ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኝ ሰው ተጠያቂነቱና በኃጢአቱ ምክንያት የሚደርስበት ቅጣት የዚያኑ ያህል የከበደ ይሆናል። ሆን ብሎ ኃጢአት የፈጸመ ግለሰብ የሚደርስበት ቅጣት ሳያውቅ ኃጢአት ከሠራው የበለጠ ይሆናል። ቅጣቶች እንደ ኃጢአተኛው የመክፈል አቅም ይለያያሉ። ይህ ዓይነቱ የአንጻራዊ መሠረታዊ ሥርዓት ከኃጢአትና ከቅጣት ሌላ የመንጻት ሥርዓትን በመሰሉ ሌሎች መስኮችም ይሠራል።—ዘሌ. 4:3, 22-28፤ 5:7-11፤ 6:2-7፤ 12:8፤ 21:1-15፤ ሉቃስ 12:47, 48፤ ያዕ. 3:1፤ 1 ዮሐ. 5:16
35 (7) ፍትሕና ፍቅር:- ለባልንጀራችን ስላለብን ግዴታ ዘሌዋውያን 19:18 ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ይናገራል። ይህ የማይዳስሰው ነገር የለም። አድልዎ ከመፈጸም፣ ከስርቆት፣ ከመዋሸት ወይም ስም ከማጥፋት ያግደናል፤ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች፣ ለድሆች፣ ለዓይነ ስውራንና መስማት ለተሳናቸው ሰዎች አሳቢነት ማሳየትን ይጠይቃል።—ዘሌ. 19:9-18፤ ማቴ. 22:39፤ ሮሜ 13:8-13
36 በተጨማሪም ኢየሱስና ሐዋርያቱ በተለይም ጳውሎስና ጴጥሮስ ከዚህ መጽሐፍ በተደጋጋሚ መጥቀሳቸው የዘሌዋውያን መጽሐፍ ለክርስቲያን ጉባኤ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” እንደሚጠቅም ማረጋገጫ ይሆናል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የጠቀሷቸው ነገሮች ብዙ ትንቢታዊ ምሳሌነት ያላቸውንና ለሚመጣው ነገር ጥላ የሆኑ ነገሮችን እንድናስተውል ይረዱናል። ጳውሎስ እንዳለው “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር . . . ጥላ አለው።” እንዲሁም “ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ” ሆኖ ያገለግላል።—2 ጢሞ. 3:16፤ ዕብ. 10:1፤ 8:5
20 የማደሪያው ድንኳን፣ የክህነቱ አገልግሎት፣ መሥዋዕቱና በተለይ ደግሞ ዓመታዊው የስርየት ቀን ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ የይሖዋን አምልኮ ከሚወክለው “ከእውነተኛይቱ ድንኳን” ጋር በተያያዘ መንገድ የእነዚህን ነገሮች መንፈሳዊ አምሳያ ለይተን እንድናውቅ ረድቶናል። (ዕብ. 8:2) ዋነኛው ካህን አሮን “ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው . . . ድንኳን” ለሚያገለግለው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። (ዕብ. 9:11፤ ዘሌ. 21:10) መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት ደም ‘የዘላለም ደህንነት ያስገኘልንን’ የኢየሱስን ደም ያመለክታል። (ዕብ. 9:12 የ1980 ትርጉም) ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን የመሥዋዕቱን ደም ለማቅረብ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገባበት የማደሪያው ድንኳን የውስጠኛው ክፍል ማለትም ቅድስተ ቅዱሳኑ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ . . . ይታይ ዘንድ” የገባበትን “የእውነተኛይቱ ምሳሌ” የሆነውን “ሰማይ” ያመለክታል።—ዕብ. 9:24፤ ዘሌ. 16:14, 15
38 ለሚቃጠል ወይም ለኃጢአት ማስተሰርያ ሆነው የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ጤነኞችና እንከን የሌለባቸው እንስሶች መሆናቸው የኢየሱስ አካል ፍጹምና ምንም እንከን የማይወጣለት መሆኑን ያመለክታል። (ዕብ. 9:13, 14፤ 10:1-10፤ ዘሌ. 1:3) ጳውሎስ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆኑ እንስሳት ከታረዱ በኋላ በድናቸው ከከተማው ውጭ ተወስዶ ስለሚቃጠልበት የስርየት ቀን ገጽታም አብራርቷል። (ዘሌ. 16:27) “ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ . . . ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብ. 13:12, 13) በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የተዘረዘሩት ሥርዓቶች ተጨማሪ ትርጉም እንዳላቸው በዚህ በመንፈስ አነሳሽነት በተሰጠ ትርጓሜ ተገልጿል። ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ብቻ ግልጽ ሊሆኑ የሚችሉትን ወደፊት ሊሆን ያላቸውን እውነተኛ ነገሮች አስቀድሞ በትንቢታዊ ጥላነት በሚያስደንቅ መንገድ መግለጹን ማስተዋል እንችላለን። (ዕብ. 9:8) ይሖዋ “በእግዚአብሔርም ቤት ላይ . . . ታላቅ ካህን” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባዘጋጀው የሕይወት ዝግጅት ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ያለውን ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው።—ዕብ. 10:19-25
39 እንደ አሮን የካህናት ቤተሰብ ሁሉ ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስም ተባባሪ የበታች ካህናት አሉት። እነዚህ ተባባሪ የበታች ካህናት “የንጉሥ ካህናት” እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል። (1 ጴጥ. 2:9) የዘሌዋውያን መጽሐፍ ይሖዋ የሾመው ታላቁ ሊቀ ካህናትና ንጉሥ የሚያከናውነውን ከኃጢአት የማንጻት ሥራ እንዲሁም ‘ደስተኛና ቅዱስ’፣ ‘የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት በመሆን ከእርሱ ጋር ለሺህ ዓመት ይነግሣሉ’ የተባለላቸው የቤተሰቡ አባላት ሊያሟሉት የሚገባውን መሥፈርት በግልጽ ከማመልከቱም በላይ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣል። ክህነታዊው አገልግሎት ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና በማድረስ ታላቅ ነገር ያከናውናል። እንዲሁም ሰማያዊው መንግሥት በምድር ላይ ሰላምንና ጽድቅን በማምጣት ደስታ ያሰፍናል! ቅዱሱ አምላክ ይሖዋ የስሙን መቀደስና የእርሱን ታላቅነት የሚያውጁ ሊቀ ካህናትና ንጉሥ እንዲሁም የንጉሥ ካህናት በማዘጋጀቱ ሁላችንም ልናመሰግነው ይገባል! በእርግጥም የዘሌዋውያን መጽሐፍ የይሖዋን መንግሥት ዓላማዎች በማሳወቁ በኩል ከሌሎቹ ‘ቅዱሳን ጽሑፎች’ ጋር በሚያስደንቅ መንገድ የተቀናጀ ነው።—ራእይ 20:6