የጥያቄ ሣጥን
◼ ድንገተኛ ሁኔታ ቢፈጠር ዝግጁ ናችሁ?
በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” ደም ለመውሰድ ግፊት የሚያሳድር ሁኔታን ጨምሮ ድንገተኛ የሕክምና ጉዳይ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። (መክ. 9:11 NW) ለእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ዝግጁ መሆን እንችል ዘንድ ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት በብዙ መንገዶች እርዳታ አድርጎልናል። ሆኖም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ይጠብቅብናል። እናንተን ለመርዳት ሲባል አስፈላጊ የሆኑት ነጥቦች በሙሉ ቀጥሎ ተዘርዝረዋል።
• የሕክምና አሰጣጥን የሚመለከት ማሳሰቢያ የያዘው እና ባለሞያዎችን ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርገው የታደሰው የሕክምና ሰነድ ምንጊዜም ከእናንተ አይለይ።
• ልጆቻችሁ የታደሰውን መታወቂያ ካርድ መያዛቸውን አረጋግጡ።
• የመስከረም 1992 የመንግሥት አገልግሎታችንን አባሪ ከልሱ። ለልጃችሁ የሚሰጠውን ሕክምና በተመለከተ ለዶክተሮችና ለዳኞች እንዴት ብላችሁ ምክንያታችሁን እንደምታስረዱ አስቀድማችሁ ተለማመዱ።
• የፕላዝማ ፕሮቲን ተዋጽኦዎችንና በደም ምትክ የሚሰጡትን መድኃኒቶች በተመለከተ የወጡትን ርዕሶች ከልሱ። (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1, 1994 ገጽ 31፤ 11-111 ገጽ 30-1፤ መጋቢት 1, 1989 (እንግሊዝኛ) ገጽ 30-1፤ ንቁ! (እንግሊዝኛ) ታኅሣሥ 8, 1994 ገጽ 23-7፤ ነሐሴ 8, 1993 ገጽ 22-5፤ ኅዳር 22, 1991 ገጽ 10፤ በተጨማሪም የመስከረም 1992 እና 11-09 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪዎችን እንድታነቡ ሐሳብ እናቀርባለን። በቀላሉ ማግኘት እንድትችሉ በፋይል አስቀምጧቸው።)
• ከሰውነት ውጪ ደም እንዲዘዋወር የሚያደርግ መሣሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል የምትፈቅዱ ከሆነ ወይም የፕላዝማ ፕሮቲን ተዋጽኦዎችን የያዙ መድኃኒቶች የምትወስዱ ከሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ አድርጉ።
• የሚቻል ከሆነ፣ ሆስፒታል ከመግባታችሁ በፊት ሽማግሌዎች ድጋፍ እንዲሰጧችሁና አስፈላጊ ከሆነም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴን (ኤች ኤል ሲ) እንዲያነጋግሩላችሁ እንደምንም ብላችሁ ለሽማግሌዎች አሳውቋቸው። ሆስፒታል የሚገባው ሕፃን ልጅ ከሆነ ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን አስቀድመው ለኤች ኤል ሲ እንዲያሳውቁ ንገሯቸው።
ደም መውሰድ የማትፈልጉ መሆናችሁን በግልጽ አሳውቁ፦ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ሕክምና ለሚሰጧቸው ዶክተሮች ደም የማይወስዱ መሆናቸውን የሚናገሩት መጨረሻ ሰዓት ላይ መሆኑን ሪፖርቶች ያሳያሉ። እንዲህ ማድረጉ በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከመሆኑም በላይ ደም የመውሰድ አደጋ ላይ ሊጥላችሁም ይችላል። ዶክተሮቹ የጸና አቋማችሁን ካወቁና ፍላጎታችሁ ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን በያዘ የተፈረመበት ሰነድ የተደገፈ ከሆነ ጊዜ ሳያባክኑ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ሲሆን በአብዛኛው ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን ለማሰብ እድል ይሰጣቸዋል።
ድንገተኛ የሕክምና ጉዳይ በማንኛውም ጊዜ በተለይ ደግሞ ባልጠበቃችሁት ወቅት ሊከሰት ስለሚችል ራሳችሁንም ሆነ ልጆቻችሁን ደም ከመውሰድ መጠበቅ እንድትችሉ ከአሁኑ ቅድመ ዝግጅት አድርጉ።—ምሳሌ 16:20፤ 22:3