የአገልግሎት ክልላችንን ለመሸፈን ድፍረት ያስፈልጋል
1 “የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2 ቆሮ. 6:2) የዓመቱን ጥቅስ የያዘው ይህ ወቅታዊ ምክር የጊዜውን አጣዳፊነት ያስታውሰናል። እንዲሁም የይሖዋን የደኅንነትና የማስጠንቀቂያ መልእክት ለሰዎች እንድናሰማ የተጣለብንን ከባድ ኃላፊነት ያስታውሰናል። በመሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎችን በማግኘት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማሰራጨት ማንኛውንም ተግባራዊ መንገድ እንጠቀማለን። በዚህ ሆነም በዚያ ሁኔታዎቹ በሚፈቅዱበት ጊዜ ሁሉ ሰዎችን ቤታቸው ሄደን በማነጋገር የአገልግሎት ክልላችንን በዘዴ ለመሸፈኑ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን።
2 ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንዶቹ ምክንያቶች ቀርበዋል:- (1) ኢየሱስ ክርስቶስና የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የተጠቀሙበት ዘዴ ነው። (ማቴ. 10:12-14፤ ሥራ 20:20) የእነርሱን ምሳሌ በመከተል እውነተኞቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናሳውቃለን። (1 ቆሮ. 11:1) (2) ይህ የስብከት ዘዴ በዘመናችን ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ሆኗል። በዚህ ሥራ መሳተፋችን ዓለም አቀፋዊ ከሆነው የወንድማማች ማኅበር ጋር ያለንን ኅብረት ያጠናክርልናል። (1 ጴጥ. 5:9) (3) በሚልዮን የሚቆጠሩ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች “ምሥራቹን” የመስማትና ከእውነተኛው አምላክ ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኙት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ስብከት አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ ይሖዋ ይህን የስብከት ዘዴ እንደባረከው ያሳያል። (4) የአገልግሎት ክልላችንን ያለማቋረጥ መሸፈናችን ሁሉም ሰዎች መልእክቱን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። መልእክቱን ለማይቀበሉ ሰዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ” ነን ብለን እንድንናገርም ያስችለናል። (ሥራ 20:20, 21, 26) (5) በዚህ ሥራ አማካኝነት አብዛኛውን ጊዜ በሌላ ቦታ የማናገኛቸውን ወይም አደባባይ ላይ ከእኛ ጋር ሲወያዩ መታየት የማይፈልጉትን ሰዎች እናገኛለን። (6) በሩን ማን ይክፈት ማን ስለማናውቅ ሁሉንም ቤቶች ማንኳኳታችን እንደማናዳላ የሚያሳይ ጥሩ መግለጫ ነው። (ሥራ 10:34) (7) ከቤት ወደ ቤት ስንመሰክር አብዛኛውን ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎችን በተሻለ መንገድ መጠቀም የሚያስችለን ሁኔታ ይኖራል። (8) በክልል መሥራት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በድጋሚ ለማግኘት የተሻለ አጋጣሚ ይሰጠናል። (9) ይህ ዘዴ አብዛኛውን ጊዜያችንን በትክክል በስብከት እንድናሳልፍ ያስችለናል። (ኤፌ. 5:15, 16) (10) በተለይ በዚህ የአገልግሎት መንገድ መሳተፋችን መንፈሳዊ ንቃታችን እንዲሁም ከይሖዋ በምናገኘው ድጋፍ ላይ ያለን ትምክህት እንዲያድግ ያደርጋል። በተጨማሪም በትሕትና እንዲሁም በሌሎች በርካታ “የአዲሱ ሰው” ገጽታዎች ረገድ ሥልጠና እናገኛለን።
3 እነዚህ ነጥቦች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የአገልግሎት ክልሎችን በመሸፈን ረገድ ቋሚ ተሳትፎ ለማድረግ ጤንነታቸው ለሚፈቅድላቸው ሁሉ አሳማኝ ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ ይህ ሥራ ተፈታታኝ ሊሆን እንደሚችል ምንም አይካድም። በሩን ማን እንደሚከፍት አለማወቃችን ፍርሃት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። ምንም እንኳ በደግነት የሚቀበሉን ወይም ቢያንስ ቢያንስ በትሕትና የሚያሰናብቱን ብዙ ሰዎች የምናገኝ ቢሆንም አንዳንድ በጣም ክፉና ጠበኛ የሆኑ ሰዎች ያጋጥሙናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ጎረቤቶችም ጣልቃ ይገባሉ። እንዲሁም ከፍተኛ አምባጓሮ የተቀሰቀሰባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይገባልን? ምሳሌያዊው እባብና ዘሮቹ የሚፈልጉት ይህንን እንደሆነ የታወቀ ነው። (ራእይ 12:17) ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ስኬታማ በሆነ መንገድ የአገልግሎት ክልሎችን መሸፈናችን ከሁሉም በላይ የተቃዋሚዎችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። እንዲያውም በበርካታ አገሮች ውስጥ ይህን የስብከት ዘዴ ለማገድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ሐዋርያትና ነቢያት፣ የማያስደስቱ ወይም አሳዛኝ የሆኑ ተሞክሮዎች ከገጠሟቸውም በኋላ በድፍረት መስበካቸውን እንዳላቆሙ ሁሉ እኛም በድፍረት የምናከናውነውን ስብከት ማዳከም የለብንም። ደስ የሚለው ነገር በአብዛኞቹ የአገልግሎት ክልሎቻችን ከቤት ወደ ቤት የመስበክ ነፃነት አለን። እንዲያውም በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ሳያሰልሱ በመካፈላቸው ጥሩ ተሞክሮዎች ያገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ያሉን ሲሆን እነርሱም ለጥረታቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ስለዚህ በክፉ መሸነፍ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንደሚደግፈን በመታመን ክፉን በመልካም ማሸነፋችንን መቀጠል አለብን። (ሮሜ 12:21፤ 1 ዮሐ. 5:4) በጽናት ከቀጠልን አሁንም ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።
4 በዚህ ሥራ ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት ማግኘት ያስፈልገናል። እንዲህ ዓይነቱ ድፍረት ከእምነታችን መጠንና ከአጠቃላዩ መንፈሳዊ ሁኔታችን ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው። ድፍረት ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል? ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። (ሥራ 4:29, 31, 33) የግል ጥናትና በስብሰባ ላይ ጥሩ ተሳትፎ ማድረግም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ውድ ለሆነው ምሥራች ስንል ስድብን ችለን ለማሳለፍ ልባችንንና አእምሯችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። (ማቴ. 5:11, 12) ተሳዳቢዎች የሚቃወሙት ለራሳቸው የሚበጃቸውን ነገር ነው። አንቀበልም ያሉት እኛን ሳይሆን እኛ መልእክተኞች ሆነን ያደረስንላቸውን የአምላክን የእውነት ቃል መሆኑን መገንዘብ እንደተሳናቸው መዘንጋት የለብንም። (2 ቆሮ. 4:3, 4) የይሖዋ መልእክተኞች መሆናችንን እንዲሁም የእርሱ ቅዱስ መንፈስና የመላእክቱ ድጋፍ እንዳለን ምንጊዜም መርሳት የለብንም። ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው ስለ ይሖዋ በድፍረት የመሰከሩ የጥንትም ሆነ ዘመናዊ የአምላክ አገልጋዮች የተዉልን ግሩም ምሳሌ አለን። ኖኅ፣ ሙሴ፣ ኤርምያስ፣ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ዕብራውያን፣ ነህምያ፣ ሐዋርያት፣ እስጢፋኖስ እንዲሁም ኢየሱስ ራሱ በእምነትና በድፍረት ረገድ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው። በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች በስደት ጊዜ የጸኑ ወንድሞቻችንም ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል።
5 አንድ ሰው ጠበኛ ወይም ሐሳበ ግትር ከሆነ በለዘበ ሁኔታ መልስ መስጠት ወይም አንዳንድ ጊዜ ወዲያውኑ ትተነው መሄድ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:17-20፤ 1 ቆሮ. 4:12፤ ቆላ. 4:6፤ ቲቶ 3:1, 2፤ ያዕ. 3:13) ንግግራችንን ለማስቆም የሚጥሩ ሰዎችን በምክንያታዊነት ማግባባት ሲባል ጠበኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር መከራከር ማለት እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ በማቴዎስ 7:6 እና 10:13 ላይ ያሉት የኢየሱስ ቃላት ተግባራዊ ይሆናሉ። ፈጽሞ ለጠብ መጋበዝ የለብንም። ኢየሱስ ሲሰድቡት መልሶ ባለመሳደብ ትክክለኛውን ምሳሌ ትቶልናል። (1 ጴጥ. 2:23) ይህን ምክር በመከተል በርካታ አስቸጋሪና መጥፎ ሁኔታዎችን ማስወገድ ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ማስተዋል ማሳየት ፈሪ ከመሆን ጋር ሊምታታብን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ ደፋር እንደነበር የታወቀ ነው፤ ይሁን እንጂ ወደ ሌላ የአገልግሎት ክልል መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘበት ጊዜ ነበር።
6 አንዳንድ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ የአገልግሎት ክልሎች በሽማግሌዎች ወይም ተሞክሮ ባላቸው ሌሎች አስፋፊዎች ቢሸፈኑ ይመረጣል። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹና የክልል አገልጋዩ ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ለየት ያለ ትኩረት መስጠት አለባቸው። በአንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎች ሦስት አስፋፊዎች አንድ ላይ ሆነው በየተራ ማገልገላቸው ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ሁለቱ በር ሲያንኳኩ አንደኛው ትንሽ ፈንጠር ብሎ ሁኔታውን መከታተል ይችላል። (ማቴ. 10:16) ሆኖም እንዲህ መደረግ ያለበት ይበልጥ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ብቻ ነው። እንዲሁም በመደዳ ያሉ ቤቶችን አንድ በአንድ ከማንኳኳት ይልቅ አንዳንድ ቤቶችን ዘሎ ሄዶ በሌላ ቀን ተመልሶ ማንኳኳት ይቻላል። አንድ የቤት ባለቤት ወደ ቤቱ እንድንመጣ የማይፈልግ መሆኑን በግልጽ ከተናገረ ይህን ቤት በማስታወሻ መዝግበን ከአገልግሎት ክልል ካርዱ ጋር ማያያዝ ይኖርብናል። (እባካችሁ፣ የሰኔ 1994 የመንግሥት አገልግሎታችንን የጥያቄ ሣጥን ተመልከቱ።)
7 የአገልግሎት ክልላችንን አንዴ ሸፍነን ከጨረስንስ? ክልሉን በድጋሚ መሸፈን ያስፈልገናል? በድጋሚ ማንኳኳት እንዳለብን የሚያሳዩ በርካታ ምክንያቶች አሉ:- (1) ወደ ክልሉ የመጡም ሆነ ከክልሉ የወጡ ሰዎች ይኖራሉ። (2) ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አመለካከታቸውን እንዲለውጡ የሚያደርጓቸው ነገሮች ይገጥሟቸዋል። ሕመም ወይም ሌላ አሳዛኝ ገጠመኝ፣ በጉዞ ላይ እያሉ ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል ከአንዱ ጋር ገንቢ የሆነ ግንኙነት ማድረጋቸው፣ የዕድሜ መግፋት፣ በአካባቢያቸው ወይም በዓለም ላይ የተፈጸሙ አስደንጋጭ ክስተቶች፣ አንድ ዓይነት ውይይት ማድረጋቸው፣ ያዩት ወይም ያነበቡት ነገር፤ እነዚህና ሌሎች ገጠመኞች የሰዎችን አስተሳሰብ ሊለውጡ ይችላሉ። (3) ብዙ ሰዎች እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት አንድ ጉዳይ ተደጋግሞ እንዲነገራቸው ይፈልጋሉ። ሌላው ቀርቶ አብዛኞቻችን፣ ለምሳሌ ያህል የቤተሰብ ጥናትን ወይም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን በተመለከተ የተሰጠንን ጠቃሚ ምክር በሥራ ከማዋላችን በፊት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ማግኘት አስፈልጎናል። (4) ከዚህ በፊት ፍላጎት ያልነበረው ሰው ሌላ የይሖዋ ምሥክር ሲያነጋግረው ደስ ሊለው ወይም አንድ ለየት ያለ አቀራረብ ሊስበው ይችላል። (5) በሌላ አጋጣሚ ላይ የቤቱ ባለቤቶች ጥሩ መንፈስ ሊኖራቸው ወይም ሰፋ ያለ ጊዜ ይኖራቸው ይሆናል። (6) ሌላ ጊዜ ስናንኳኳ ከዚህ በፊት ያላገኘነውን የቤተሰቡን አባል እናገኝ ይሆናል። (7) ብዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ተጠራጣሪዎች ቢሆኑም በኋላ ግን ደጋግመው ላገኙዋቸው ሰዎች ፈታ ማለት ይጀምራሉ። (8) የቤቱን ባለቤቶች ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ የተለያዩ ጽሑፎች አሉን። (9) ቤታቸው እየሄድን ማነጋገራችንን በመቀጠል የፍርድ ጊዜ ሲመጣ፣ ወዲያውኑ ተስፋ ቆርጣችሁ ትታችሁናል ብለው እንደማይወቅሱን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (10) በሥራው በመቀጠል የሰዎችን ቸልተኝነት በመልካም ማሸነፋችንን እንቀጥላለን።
8 ስለዚህ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ጤንነታችን የሚፈቅድልን ሁሉ የአገልግሎት ክልል ለመሸፈን በየወሩ ወይም የሚቻል ከሆነ በየሳምንቱ የተወሰነ ጊዜ እንመድብ። እንዲህ ማድረጋችን ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እንድናቀርብ ይረዳናል። በይሖዋ በመታመን ድፍረት ማግኘት እንችላለን። (2 ቆሮ. 6:4, 8፤ ፊልጵ. 1:27, 28፤ ዕብ. 13:6) መንፈሳዊ እድገት እናደርጋለን፤ እንዲሁም ተጨማሪ በረከት እናገኛለን።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል7]
(ገጽ 8 ላይ ይቀጥላል)
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል8]
ድፍረት . . . (ከገጽ 7 የዞረ)