1 ስብሰባዎች ለመንፈሳዊ ደህንነታችን የግድ አስፈላጊ ናቸው። ከስብሰባዎች የምናገኘው ደስታ ከስብሰባው በፊት፣ በስብሰባው ወቅትና ስብሰባው ካለቀ በኋላ ከምናደርጋቸው ነገሮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ከስብሰባዎች የምናገኘው ደስታ እንዳይቀንስ ጠብቀን ለማቆየት ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ከስብሰባዎች በፊት፦ ዝግጅት ከስብሰባዎች በምናገኘው ደስታ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው። በጥሩ ሁኔታ ከተዘጋጀን ትኩረት ሰጥተን ለመከታተልና ተሳትፎ ለማድረግ የበለጠ እንነሳሳለን። ከዚህም በተጨማሪ ክፍል እንድናቀርብ ከተመደብን በመመሪያው መሠረት መልእክቱን በትክክል የማስተላለፍና አድማጮችን በሚማርክ መንገድ የማቅረብ ዓላማ በመያዝ በሚገባ መዘጋጀትና በጥንቃቄ መለማመድ ይኖርብናል። ሁላችንም ጥቅም የምናገኝባቸው ስብሰባዎች የሚያነቃቁና የሚያንጹ እንዲሆኑ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ስናደርግ መንፈሳዊ እድገታችን በግልጽ ከመታየቱም በላይ ከፍተኛ ደስታ እናገኛለን።—1 ጢሞ. 4:15, 16
3 በስብሰባዎች ወቅት፦ በስብሰባዎች ወቅት ሐሳብ በመስጠት መሳተፋችን ኘሮግራሙ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልን ያደርጋል። የአድማጮችን ተሳትፎ የሚጠይቁ የስብሰባ ክፍሎች የሁሉም የጉባኤው አባላት ክፍል እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ መልሶች እጥር ምጥን ያሉና ነጥቡን የሚያስጨብጡ ሲሆኑ ውጤታቸው የጎላ ይሆናል። የሚያንጹ ተሞክሮዎች በአጭሩ መናገራችን በጣም የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ሊሆን ይችላል። በተለይ ክፍሉ እንደዚያ እንድናደርግ የሚጠይቅ ከሆነ ለመናገር ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። (ምሳሌ 15:23፤ ሥራ 15:3) በስብሰባዎች ላይ ክፍል ሲሰጠን በግለትና እንደምናምንበት በሚያሳይ መንገድ በመናገር ትምህርቱን አስደሳች በሆነ፣ ባልተጋነነና ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መንገድ ማቅረብ ይገባናል።
4 ከስብሰባዎች በኋላ፦ ከሌሎች ጋር የደግነት ቃላትና ወዳጃዊ ሰላምታ መለዋወጥ እንዲሁም በስብሰባዎቹ ላይ በቀረቡት ጥቂት ቁልፍ የሆኑ ነጥቦች ላይ መወያየት ሁላችንንም ይጠቅመናል። ትንንሽ ልጆች፣ በእድሜ የገፉ እንዲሁም አዲሶች በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠታቸው እንደተደሰትን ስንገልጽላቸው የወንድማማችነት ፍቅራችን ይበልጥ ጠንካራ ይሆናል። አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የማይገኙትን ወንድሞችና እህቶች ከመተቸት ይልቅ እኛ በስብሰባዎች ላይ በመገኘታችን ያገኘነውን ደስታ ልናካፍላቸው ይገባል። ይህን ስናደርግ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙ እናበረታታቸዋለን።—ዕብ. 10:24, 25
5 ይህን የመሰለው እርስ በርስ ለመበረታታት የግድ አስፈላጊ የሆነ ዝግጅት እንዲያመልጠን አንፍቀድ። (ሮሜ 1:11, 12) ሁላችንም ትጋት የታከለበት ልባዊ ጥረት በማድረግ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የምናገኘውን ደስታ ጠብቀን ለማቆየት እንችላለን።