የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 11/99 ገጽ 3-4
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር 5—ዘዳግም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር 5—ዘዳግም
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
የመንግሥት አገልግሎታችን—1999
km 11/99 ገጽ 3-4

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 5​—ዘዳግም

ጸሐፊው፦ ሙሴ

የተጻፈበት ቦታ፦ በሞዓብ ሜዳ

ተጽፎ ያለቀው፦ 1473 ከዘአበ

የሚሸፍነው ጊዜ፦ 2 ወር (1473 ከዘአበ)

የዘዳግም መጽሐፍ ለይሖዋ ሕዝቦች ይህ ነው የማይባል ጠቃሚ መልእክት ይዞላቸዋል። የእስራኤል ልጆች ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ከተንከራተቱ በኋላ አሁን በተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ ቆመዋል። ከፊታቸው ምን ይጠብቃቸው ይሆን? ከዮርዳኖስ ማዶ ምን የተለየ ችግር ይገጥማቸው ይሆን? ሙሴ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝቡ ምን የሚናገረው ነገር ይኖረው ይሆን? በተጨማሪም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

2 የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አምስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘዳግም መጽሐፍ ተመዝግበው በሚገኙት የሙሴ ቃላት ውስጥ ይገኛል። በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ዘገባዎች ቀደም ካሉት መጻሕፍት የተወሰዱ ቢሆንም ዘዳግም ጠቃሚ የሚያደርገው የራሱ ገጽታ አለው። ለምን እንደዚያ እንላለን? የይሖዋ ሕዝቦች ጠንካራና አስተማማኝ መመሪያ አስፈልጓቸው በነበረበት ወቅት የተሰጠ በመሆኑ ለመለኮታዊ መልእክት አጽንዖት የሚሰጥ ነው። በአዲስ መሪ ሥር ሆነው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበዋል። ወደፊት ለመግፋት ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ በረከት የሚመራ ትክክለኛ ጎዳና መከተል ይችሉ ዘንድ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር።

3 ከዚህ ጋር በመስማማት ሙሴ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት እስራኤላውያን ታዛዥና ታማኝ እንዲሆኑ በቀጥታ አሳስቧቸዋል። በጠቅላላው መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የሚጠይቅና ሕዝቦቹ ‘በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ኃይላቸው እርሱን እንዲወዱት’ የሚፈልግ ልዑል አምላክ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። እርሱ “የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፣ በፍርድ የማያዳላ፣ መማለጃም የማይቀበል” ነው። ይሖዋ የሚቀናቀነውን አይታገሥም። እርሱን መታዘዝ ሕይወት የሚያስገኝ ሲሆን እርሱን አለመታዘዝ ደግሞ ሞት ያስከትላል። በዘዳግም ላይ የሰፈረው የይሖዋ መመሪያ እስራኤላውያን ወደፊት ለሚጠብቃቸው እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሥራ የሚያዘጋጃቸውና ምክር የሚለግሳቸው ነበር። እኛም ብንሆን በይሖዋ ፍርሃት መጓዛችንን እንድንቀጥልና ብልሹ በሆነው ዓለም ውስጥ ስሙን መቀደሳችንን መቀጠል እንችል ዘንድ በዛሬው ጊዜ የሚያስፈልገንን ምክር ይዞልናል።​—ዘዳ. 5:9, 10፤ 6:4-6፤ 10:12-22

4 ዘዳግም የሚለው ስያሜ የመጣው ዲዩተሮኖሚኦን ከሚለው የግሪኩ የሰፕቱጀንት ትርጉም ሲሆን ቃሉም “ሁለተኛ” የሚል ትርጉም ካለው ዲዩተሮስ እና “ሕግ” የሚል ትርጉም ካለው ኖሞስ ከሚሉት ቃላት የተገኘ ነው። ስለዚህ ዘዳግም ማለት “ሁለተኛ ሕግ፤ የሕጉ መደጋገም” ማለት ነው። ይህም ዘዳግም 17:18 ላይ ከሚገኘው ሚሽኔህ ሃትቶህራህ ከሚለው የዕብራይስጡ ሐረግ የግሪክኛ ትርጉም የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ‘የሕጉ ቅጂ’ ማለት ነው። የስሙ ትርጉም ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ዘዳግም እንደ ሁለተኛ ሕግ ወይም እንዲሁ ድግግሞሽ እንደሆነ ተደርጎ መታየት አይኖርበትም። ከዚያ ይልቅ እስራኤላውያን በቅርቡ በሚወርሷት የተስፋይቱ ምድር ውስጥ ይሖዋን እንዲወዱና እንዲታዘዙ ለማሳሰብ የተሰጠ የሕጉ ማብራሪያ ነው።​—1:5

5 መጽሐፉ የፔንታቱች አምስተኛ ጥቅል ወይም መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ጸሐፊውም ከእርሱ በፊት ያሉትን አራት መጻሕፍት የጻፈው ሙሴ መሆን አለበት። የመክፈቻው ዓረፍተ ነገር “ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል” በማለት ዘዳግምን ያስተዋውቃል። በሌላም ቦታ “ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ” የሚለውና “ሙሴም . . . ይህችን መዝሙር ጻፈ” የሚሉት አነጋገሮች ጸሐፊው ሙሴ መሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጡ ናቸው። የሙሴ ስም በመጽሐፉ ውስጥ 40 ጊዜ ያህል ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው ዓረፍተ ነገሮቹን እርሱ በቀጥታ እንደተናገራቸው ተደርገው ተገልጸዋል። በአብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል ሙሴ በአንደኛ መደብ ተገልጿል። የመጨረሻዎቹ ቁጥሮች ሙሴ ከሞተ በኋላ የተጨመሩ ሲሆኑ ኢያሱ ወይም ሊቀ ካህኑ አልአዛር ሳይጨምሯቸው አልቀረም።​—1:1፤ 31:9, 22, 24-26

6 በዘዳግም ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች የተከናወኑት መቼ ነው? መጽሐፉ ራሱ ገና ሲጀምር “በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን” በማለት ይናገራል። የዘዳግም መጽሐፍ ሲጠናቀቅ የኢያሱ መጽሐፍ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ከመሻገራቸው ሦስት ቀን ቀደም ብሎ ከነበረው ታሪክ በመነሳት ይቀጥላል። ይህም የሆነው “በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን” ላይ ነው። (ዘዳ. 1:3፤ ኢያሱ 1:11፤ 4:19) ይህም በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ነገሮች የተከናወኑት በሁለት ወር ከአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ከዘጠኝ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 30 ቀኖቹ ያለፉት ለሙሴ ሞት በተደረገው ለቅሶ ነው። (ዘዳ. 34:8) ይህም ማለት በዘዳግም ውስጥ የሚገኙት ክንውኖች የተፈጸሙት በ40ኛው ዓመት በ11ኛው ወር ላይ ነው ለማለት ይቻላል። ሙሴ የሞተው በ40ኛው ዓመት በ12ኛው ወር ወይም በ1473 ከዘአበ መግቢያ ላይ ስለሆነ በ11ኛው ወር መጨረሻ ላይ መጽሐፉም ተጽፎ አልቋል ብሎ መናገር ይቻላል።

7 የፔንታቱች ክፍል ለሆኑት ለመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት ትክክለኝነት የተሰጡት ማስረጃዎች አምስተኛ መጽሐፍ ለሆነው ለዘዳግም መጽሐፍም ይሠራሉ። እንዲሁም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑ አራት መጻሕፍት መካከል አንደኛው ዘዳግም ሲሆን ሦስቱ ደግሞ ዘፍጥረት፣ መዝሙርና ኢሳይያስ ናቸው። በዚህ መልኩ 83 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል ከዘዳግም መጽሐፍ ምንም ሳይጠቅሱ ያለፉት ስድስት መጻሕፍት ብቻ ናቸው።a

8 ኢየሱስ ራሱ የዘዳግምን መጽሐፍ የሚደግፍ ከሁሉ ይበልጥ ጠንካራ ምሥክርነት ሰጥቷል። አገልግሎቱን ገና እንደጀመረ ዲያብሎስ ሦስት ፈተናዎች አቅርቦለት የነበረ ሲሆን ሦስቱንም ጊዜ “ተጽፎአል” በማለት መልስ ሰጥቶታል። የት ነው የተጻፈው? በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ነዋ። (8:3፤ 6:16, 13) ኢየሱስ ይህን መጽሐፍ እንደ ባለ ሥልጣን አድርጎ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።” “ጌታን አምላክህን አትፈታተነው።” “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ።” (ማቴ. 4:1-11) ከጊዜ በኋላ ፈሪሳውያን የአምላክን ትእዛዛት በተመለከተ ፈተና ባቀረቡለት ጊዜ ኢየሱስ “ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ” በማለት መልስ የሰጠው ከዘዳግም 6:5 ላይ በመጥቀስ ነበር። (ማቴ. 22:37, 38፤ ማር. 12:30፤ ሉቃስ 10:27) ኢየሱስ የሰጠው ምሥክርነት የዘዳግም መጽሐፍ ትክክለኛ ዘገባ መሆኑን በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጥ ነው።

9 ከዚህም በተጨማሪ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ክንውኖችን መግለጫዎች ከታሪካዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎቹ ጋር በትክክል የሚስማሙ ናቸው። ስለ ግብፅ፣ ከነዓን፣ አማሌቅ፣ አሞን፣ ሞዓብ እና ኤዶም የተጠቀሱት ነገሮች በጊዜው ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ከመሆናቸውም በላይ የቦታ ስሞች በትክክል ተገልጸዋል።b የአርኪኦሎጂ ውጤቶች የሙሴን ጽሑፍ ተዓማኒነት የሚያረጋግጡ ተደጋጋሚ ማረጋገጫዎችን በየጊዜው መስጠታቸውን ቀጥለዋል። ሄነሪ ኤች ሃሌይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “[ሙሴ ፔንታቱችን ጽፏል] የሚለውን የቆየ አባባል የሚያጠናክሩ የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ከጊዜ በኋላ በብዛት በመገኘት ላይ ናቸው። በሙሴ ዘመን ጽሑፍ አይታወቅም ነበር የሚለው አስተያየት ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው። እንዲሁም በየዓመቱ በግብፅ፣ በፍልስጥኤም እና በሜሶጶጣሚያ የሚገኙት የተቀረጹ ጽሑፎችና የምድር ንብር ማስረጃዎች [የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች] እውነተኛ ታሪካዊ ዘገባ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው። እንዲሁም ‘ምሁራን’ ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ የሚገልጸውን ከጥንት የነበረ ሃቅ ለመቀበል እየተገደዱ ነው።”c ስለዚህ የውጭ ማስረጃዎች እንኳን ሳይቀሩ ዘዳግምም ሆነ የቀሩት የፔንታቱች ክፍሎች በነቢዩ ሙሴ የተጻፉ እውነተኛና ትክክለኛ ዘገባዎች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

30 የፔንታቱች የመጨረሻ ክፍል የሆነው ዘዳግም ታላቁን የይሖዋ አምላክ ስም በማወጅና በመቀደስ ረገድ የቀደሙት ጽሑፎች የተናገሩትን ጠቅለል አድርጎ የያዘ መጽሐፍ ነው። ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲሰጠው የሚፈልግና በአጋንንት አማልክት የሚመራ የሐሰት ሃይማኖታዊ አምልኮን በቸልታ የማይመለከት አምላክ ነው። በዚህ በእኛ ዘመን የሚኖሩ ሁሉም ክርስቲያኖች ለአምላክ ሕግ መሠረት ለሆኑት ታላላቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የበለጠ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፤ እንዲሁም ጠላቶቹን ለማጥፋት አንጸባራቂ ሰይፉን በሚሰነዝርበት ወቅት ከእርግማኑ ለመትረፍ እርሱን መታዘዝ ይኖርባቸዋል። “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” የሚለው ታላቁና ፊተኛው ትእዛዝ በሕይወታቸው ውስጥ እንደ ምልክት ሆኖ ሊመራቸው ይገባል።​—6:5

31 የተቀሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ከዘዳግም መጽሐፍ በተደጋጋሚ በመጥቀስ ስለ መለኮታዊ ዓላማዎች ያለንን ግንዛቤ ከፍ እንድናደርግ ይረዱናል። ኢየሱስ ለፈታኙ መልስ ለመስጠት ከጠቀሳቸው ጥቅሶች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ጥቅሶችንም ጠቅሷል። (ዘዳ. 5:16​—ማቴ. 15:4፤ ዘዳ. 17:6​—ማቴ. 18:16 እና ዮሐ. 8:17) ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ በይሖዋ የትንቢት ጥቅል ውስጥ አንዳች መጨመርም ሆነ ከእርሱ መቀነስ ተገቢ አለመሆኑን ለማስጠንቀቅ ከዘዳግም መጽሐፍ ጠቅሶ ተናግሯል። (ዘዳ. 4:2​—ራእይ 22:18) ጴጥሮስ፣ ይሖዋ በእስራኤል መካከል አስነሳለሁ ብሎ ቃል የገባው ታላቅ ነቢይና ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመበትን ኃይለኛ የመከራከሪያ ነጥብ ያገኘው ከዘዳግም መጽሐፍ ነው። (ዘዳ. 18:15-19​—ሥራ 3:22, 23) ጳውሎስ ለሠራተኛ ደሞዙ እንደሚገባ፣ ምሥክሮች የሚሰጡትን ቃል በጥንቃቄ ስለ መመርመር እንዲሁም ልጆችን የሚመለከት መመሪያ የሰጠው ከዚሁ መጽሐፍ በመጥቀስ ነው።​—ዘዳ. 25:4​—1 ቆሮ. 9:8-10 እና፤ 1 ጢሞ. 5:17, 18፤ ዘዳ. 13:14 እና ዘዳ 19:15​—1 ጢሞ. 5:19 እና፤ 2 ቆሮ. 13:1፤ ዘዳ. 5:16​—ኤፌ. 6:2, 3

32 ከዘዳግም መመሪያና ማበረታቻ ያገኙት የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖሩ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮችም ናቸው። እኛም የእነርሱን ምሳሌ ብንከተል ጥሩ ነው። አካን እንዳደረገው እርም ከሆኑት ነገሮች አንድም ነገር ሳይነካ ከነዓን በተወረረችበት ወቅት ድል የተደረጉትን ከተማዎች በሙሉ በማጥፋት ረገድ በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ ያሳየውን ልባዊ ታዛዥነት ተመልከት። (ዘዳ. 20:15-18 እና ዘዳ 21:23​—ኢያሱ 8:24-27, 29) ጌዴዎን ‘የፈራውንና የደነገጠውን’ ከሠራዊቱ መካከል ማሰናበቱ ለሕጉ ያለውን ታዛዥነት የሚያሳይ ነበር። (ዘዳ. 20:1-9​—መሳ. 7:1-11) በእስራኤልና በይሁዳ የነበሩት ነቢያት በይሖዋ ሕግ ላይ የነበራቸው እምነት በክፉዎቹ አሕዛብ ላይ የውግዘት ቃል እንዲናገሩ አድርጓቸዋል። በዚህ ረገድ አሞጽ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። (ዘዳ. 24:12-15​—አሞጽ 2:6-8) በእርግጥም የዘዳግምን መጽሐፍ ከተቀረው የአምላክ ቃል ጋር የሚያዛምዱ ቃል በቃል በመቶ የሚቆጠሩ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ይህም ከተቀረው የአምላክ ቃል ጋር ስምምና ጠቃሚ መሆኑን ያሳያል።

33 የዘዳግም መጽሐፍ ልዑሉን አምላክ ይሖዋን ያወድሳል። በመላው መጽሐፍ ውስጥ ‘ይሖዋን ማምለክና፣ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ መስጠት’ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ምንም እንኳ ሕጉ በክርስቲያኖች ላይ የሚሠራ ባይሆንም በውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች አልተሻሩም። (ገላ. 3:19) በሚሰጠው የላቀ ደረጃ ያለው ትምህርት፣ በፍጹም ግልጽነቱና ቀለል ባለው ማብራሪያው እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዚህ የአምላክን ሕግ ከያዘው ኃይለኛ መጽሐፍ ብዙ ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ! ሌላው ቀርቶ የዓለም ብሔራት እንኳ ሳይቀሩ የይሖዋ ታላቅ ሕግ ያለውን የበላይነት ከመገንዘባቸው የተነሳ ዘዳግም ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ደንቦችን በመውሰድ በራሳቸው የሕግ መጽሐፍ ላይ ገልብጠዋቸዋል።

34 ከዚህም በላይ ይህ የሕጉ ማብራሪያ ወደ አምላክ መንግሥት የሚያመለክትና ለመንግሥቱ ያለንን ግንዛቤ ከፍ የሚያደርግ ነው። እንዴት? ዕጩው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር በነበረበት ወቅት ከመጽሐፉ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጥቀሱ ከመጽሐፉ ጋር ጥልቅ ትውውቅ የነበረው ከመሆኑም በላይ እንደሠራበት የሚያሳይ ነው። ንጉሣዊ አገዛዙን በመላው ምድር ላይ ሲያሰፍን ግዛቱ በዚህ “ሕግ” ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ይሆናል፤ እንዲሁም የመንግሥት “ዘር” እንደመሆኑ መጠን በእርሱ አማካኝነት ራሳቸውን ለመባረክ የሚፈልጉ ሁሉ ለእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መታዘዝ ይኖርባቸዋል። (ዘፍ. 22:18፤ ዘዳ. 7:12-14) ለእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከአሁኑ ጀምሮ ታዛዥ መሆን ጠቃሚ ነው። ይህ 3,500 ዓመት ያስቆጠረ ሕግ ፈጽሞ ዘመን አልሻረውም። ይልቁንም ዛሬም በጎላ ድምፅ ይናገራል። ወደፊትም በአምላክ መንግሥት አዲስ ዓለም መናገሩን ይቀጥላል። የይሖዋ ሕዝቦች በፔንታቱች ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ መመሪያዎች በተግባር በማዋል የይሖዋን ስም መቀደሳቸውን እንዲቀጥሉ ምኞታችን ነው። ይኸው ጉዳይ በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። በእርግጥም ዘዳግም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ‘የቅዱሳን ጽሑፎች’ ክፍል የሆነ መጽሐፍ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በቢ ኤፍ ዌስትኮት እና በኤፍ ጄ ኤ ሆርት በ1956 የተዘጋጀውን ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ኦሪጂናል ግሪክ በተባለው መጽሐፍ ገጽ 601-18 ላይ የሚገኘውን “ከብሉይ ኪዳን የተወሰዱ ጥቅሶች” የሚለውን ዝርዝር ተመልከት።

b ዘዳግም 3:9 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።

c በሄንሪ ኤች ሃሊ የተዘጋጀው ሃሌይስ ባይብል ሃንድቡክ፣ 1988 ገጽ 56

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ