በእምነት ጸንተን ለመቆም ምን ሊረዳን ይችላል?
1 ከይሖዋ ድርጅት ጋር መተባበር ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ያደረግነው መንፈሳዊ እድገት ለደስታ ምንጭ እንደሆነልን የተረጋገጠ ነው! ሆኖም ‘ሥር ሰድደን፣ ታንጸንና በእምነት ጸንተን’ ለመቆየት የማያቋርጥ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አስፈላጊ ነው። (ቆላ. 2:6, 7) ብዙዎች በመንፈሳዊ ሲበለጽጉ አንዳንዶች ግን ‘በእምነት ጸንተው መቆም’ ስላልቻሉ ተንሸራትተዋል። (1 ቆሮ. 16:13 የ1980 ትርጉም ) እኛም ተመሳሳይ ነገር እንዳይደርስብን መከላከል እንችላለን። እንዴት?
2 የማያቋርጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ:- በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጥሩ የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ልማድ አዳብሩ። በድርጅቱ አማካኝነት መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን የሚያሟሉ የተትረፈረፉ ነገሮች ይቀርቡልናል። ከጉባኤ፣ ከልዩ፣ ከወረዳና ከአውራጃ ስብሰባዎች የሚገኘውን ጥቅም ለመቅሰም አዘውትረን የምንገኝ ከሆነ የበለጠ መንፈሳዊ እድገትና ጥንካሬ እንዲኖረን ይረዱናል። (ዕብ. 10:24, 25) መጽሐፍ ቅዱስን፣ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም የአምላክን ቃል ጠንካራ ምግብ የሚያብራሩትን መጽሐፎች ዘወትር የማንበብ ልማድ ካለን መንፈሳዊ ሥሮቻችን ጥልቅና ጠንካሮች ይሆናሉ። (ዕብ. 5:14) መንፈሳዊ ግቦች የምናወጣና ግቦቻችን ላይ ለመድረስ የምንጣጣር ከሆነ ዘላቂ ጥቅም እናገኛለን።—ፊልጵ. 3:16
3 ከጎለመሱ ሰዎች የሚገኝ ዕርዳታ:- በጉባኤ ውስጥ ካሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎች ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማስፋት ጣር። ሽማግሌዎች እኛን የማበርታት ተቀዳሚ ኃላፊነት ስለተቀበሉ ቀርበህ ተዋወቃቸው። (1 ተሰ. 2:11, 12) የሚሰጡህን ምክር ወይም ሐሳብ ሁሉ ተቀበል። (ኤፌ. 4:11-16) የጉባኤ አገልጋዮችም ቢሆኑ ሌሎች በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት የሚፈልጉ ወንድሞች ስለሆኑ ማበረታቻ በምትፈልግበት ጊዜ ወደ እነርሱም መሄድ ትችላለህ።
4 በአገልግሎትህ ረገድ እርዳታ ያስፈልግሃል? ሽማግሌዎችን ቀርበህ እርዳታ ጠይቅ። ምናልባት አንተም አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ በሚለው ዝግጅት ውስጥ ልትታቀፍ ትችላለህ። የተጠመቅኸው በቅርቡ ነውን? አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ማጥናትና ትምህርቱን ተግባራዊ ማድረግ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንድትደርስ ያንቀሳቅስሃል። ወላጅ ነህን? የልጆችህን መንፈሳዊነት ያለማሰለስ አጠናክር።—ኤፌ. 6:4
5 ሥር በመስደድና በእምነት ጸንተን በመቆም ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት መፍጠር እንችላለን። እንዲህ በማድረግ የሰይጣንን ጥቃት መቋቋምና የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋችንን ማጠንከር እንችላለን።—1 ጴጥ. 5:9, 10