‘ቃሉን በጥድፊያ ስሜት ስበኩ’
1 “አጣዳፊ ጉዳይ” የሚል መልእክት የተጻፈበት ነገር ቢደርስህ ምን ይሰማሃል? “አጣዳፊ” የሚለው ቃል “አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ” ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘ቃሉን በጥድፊያ ስሜት እንዲሰብኩ’ ያሳሰበበት ጥሩ ምክንያት ነበረው። (2 ጢሞ. 4:2 NW) አንተስ ለሥራው አፋጣኝ ትኩረት በመስጠት ለዚህ ማሳሰቢያ ምላሽ ትሰጣለህን?
2 ጳውሎስ አንዳንድ ወንድሞቹ በክርስቲያናዊ ‘ሥራቸው ከመትጋት የመለገም’ አዝማሚያ እንዳሳዩ ሪፖርት ደርሶት ይሆናል። (ሮሜ 12:11) ይህ ደግሞ ከሥራቸው ያገኙት የነበረው ውጤትና ሌሎችን በመርዳት ማግኘት ይችሉ የነበረው ደስታ ውስን እንዲሆን አድርጎባቸዋል።
3 ኢየሱስ ለአገልግሎት የነበረው አመለካከት:- ኢየሱስ አገልግሎቱን በማከናወን ያገኘው ደስታ የላቀ ነበር። “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ሲል ተናግሯል። ‘እርሻው ለመታጨድ ደርሷል’ ብሎ ላበረታታቸው ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስ ምሳሌነት ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ሆኖላቸዋል። (ዮሐ. 4:34, 35) ኢየሱስ “የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ መናገሩ በአገልግሎት ዘመኑ በሙሉ ያሳየውን የጥድፊያ ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው። (ማቴ. 9:38) ኢየሱስ ተልዕኮው ስብከት መሆኑን በመገንዘቡ ምንም ነገር ይህን ከመፈጸም እንዲያግደው አልፈቀደም።
4 እኛስ? ዛሬ በስብከቱ ሥራ ወደፊት የመግፋቱ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የጥድፊያ ስሜት የሚጠይቅ ሆኗል። በአብዛኛው የምድር ክፍል አዝመራው ለአጨዳ ደርሷል። በእኛ አካባቢ ገና ያላነጋገርናቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። የተጣራ ምስክርነት ተሰጥቶባቸዋል ተብሎ በሚታሰብባቸው አካባቢዎች እንኳን በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጠመቁ ነው። የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ‘የጌታ ሥራ በዝቷል።’ (1 ቆሮ. 15:58) ከየትኛውም ጊዜ ይበልጥ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ለማካፈል ብርቱ ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።
5 ከቤት ወደ ቤትም ሆነ በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ ሰዎች በሚገኙበት በማንኛውም ቦታ ምሥራቹን ለሌሎች ለማዳረስ እንትጋ። በተቻለን መጠን በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን እንደምናስቀድም በግልጽ ማሳየት እንችላለን። (ማቴ. 6:33) ቃሉን በጥድፊያ ስሜት በመስበክ የምናሳየው ታማኝነት ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል።