የጥያቄ ሣጥን
◼ ተወግዶ የነበረ አንድ ሰው መመለሱ በማስታወቂያ ሲነገር ማጨብጨብ ተገቢ ነውን?
ይሖዋ አምላክ በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ሞገሱን መልሰው እንዲያገኙና ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንዲመለሱ በቅዱስ ጽሑፉ አማካኝነት ሁኔታውን አመቻችቷል። (መዝ. 51:12, 17) ከልብ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ከውገዳ ሲመለሱ ፍቅራችንን እንድናረጋግጥላቸው ማበረታቻ ተሰጥቶናል።—2 ቆሮ. 2:6-8
አንድ ዘመዳችን ወይም የምናውቀው ሰው ከውገዳ ሲመለስ በጣም የምንደሰት ቢሆንም እንኳን የሰውዬው ከውገዳ መመለስ በጉባኤ ማስታወቂያ በሚነገርበት ጊዜ ተገቢ ዓይነት ሁኔታ ሊንጸባረቅ ይገባል። የጥቅምት 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17 ስለ ሁኔታው እንደዚህ ይላል:- “ይሁን እንጂ አብዛኛው የጉባኤው አባል ሰውየው እንዲወገድ ወይም እንዲመለስ ያደረጉት ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ለይቶ እንደማያውቅ መዘንጋት የለብንም። በተጨማሪም ንስሐ የገባው ሰው ቀደም ሲል በሠራው ስህተት ምክንያት በግል የተነኩ ወይም የተጎዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባትም ይህ ሁኔታ ዘላቂ ጉዳት አስከትሎባቸው ይሆናል። ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ስለምናስገባ ከውገዳ መመለስን የሚገልጽ ማስታወቂያ በሚነገርበት ጊዜ ደስታችንን የሚገልጹ ነገሮች ከማድረግ እንቆጠባለን። ከዚህ ይልቅ ለግለሰቡ በግል ስሜታችንን ልንገልጽ እንችላለን።”
አንድ ሰው ወደ እውነት ሲመለስ በጣም ብንደሰትም እንኳን የመመለሱ ወይም የመመለሷ ማስታወቂያ በሚነገርበት ጊዜ ማጨብጨብ ተገቢ አይሆንም።