የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 6—ኢያሱ
ጸሐፊው፦ ኢያሱ
የተጻፈበት ቦታ፦ ከነዓን
ተጽፎ ያለቀው፦ 1450 ከዘአበ ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ፦ 1473 ከዘአበ -1450 ገደማ
ዓመቱ 1473 ከዘአበ ነው። ትዕይንቱ እጅግ አስገራሚና ልብ የሚያንጠለጥል ነው። በሞዓብ ሜዳ የሰፈሩት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ማለትም ወደ ከንዓን ለመግባት ተዘጋጅተዋል። ከዮርዳኖስ ባሻገር ያለው ክልል እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ሠራዊት ባላቸው በርካታ ትናንሽ መንግሥታት የተያዘ ነው። እነዚህ መንግሥታት እርስ በርሳቸው የተከፋፈሉና ለዓመታት በዘለቀው የግብፅ ብልሹ አገዛዝ የተዳከሙ ናቸው። ሆኖም ለእስራኤል ብሔር እንዲህ በዋዛ የሚቀመሱ አልነበሩም። ምድሪቱን ለመቆጣጠር እንደ ኢያሪኮ፣ ጋይ፣ አሶር እና ለኪሶ ያሉት በቅጥር የተከበቡ ከተሞች ድል መደረግ ነበረባቸው። ከፊታቸው ወሳኝ የሆነ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። ወሳኝ የሆኑ ውጊያዎች መካሄድ የነበረባቸው ሲሆን ይሖዋም አስገራሚ ተዓምራት በማድረግ ለሕዝቡ ሲል እጁን ጣልቃ በማስገባት በምድሪቱ ላይ አሰፍራችኋለሁ በማለት የገባውን ቃል ይፈጽማል። ይሖዋ ሕዝቡን ስለያዘበት መንገድ የሚገልጹት እነዚህ ስሜት ቀስቃሽ ክንውኖች የዓይን ምሥክር በሆነ አንድ ሰው በጽሑፍ እንደሚሰፍሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህንንም ለማድረግ ይሖዋ የሙሴ ተተኪ አድርጎ ከሾመው ከኢያሱ የተሻለ ሌላ ማን ሊኖር ይችላል!—ዘኁ. 27:15-23
2 ኢያሱ መሪ እንዲሆንና ሊፈጸም ያለውን ክንውን እንዲጽፍ መመረጡ የተገባ ነው። ቀደም ሲል ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በቆዩበት ጊዜ የሙሴ የቅርብ ተባባሪ ሆኖ ሠርቷል። “ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ ”ሆኖ መሥራቱ በመንፈሳዊ እንዲጎለምስና ሠራዊቱን የመምራት ብቃት እንዲያገኝ አድርጎታል። (ዘኁ. 11:28፤ ዘጸ. 24:13፤ 33:11፤ ኢያሱ 1:1) እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው በወጡበት ዓመት በ1513 ከዘአበ አማሌቃውያን ድል በተነሱበት ጦርነት የእስራኤል ጦር መሪ ሆኖ ሠርቷል። (ዘጸ. 17:9-14) የከነዓንን ምድር የመሰለል ከባድ ተልእኮ ለመቀበል ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው በተመረጠ ጊዜ ኢያሱ ታማኝ የሙሴ አገልጋይና ደፋር የጦር አዛዥ እንደመሆኑ መጠን ከኤፍሬም ነገድ መመረጡ የሚጠበቅ ነገር ነበር። በዚያን ወቅት ያሳየው ድፍረትና ታማኝነት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚገባ ማረጋገጫ ሆኖለታል። (ዘኁ. 13:8፤ 14:6-9, 30, 38) አዎን፣ ኢያሱ የተባለው ይህ የነዌ ልጅ “መንፈስ ያለበት፣“ ’እግዚአብሔርን ፈጽሞ የተከተለና’ ’የጥበብን መንፈስ የሞላበት’ ሰው ነው። “ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ . . . እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ“ ተብሎ መነገሩ ምንም አያስደንቅም።—ዘኁ. 27:18፤ 32:12፤ ዘዳ. 34:9፤ ኢያሱ 24:31
3 ኢያሱ ያገኘው ተሞክሮና ሥልጠና እንዲሁም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ በመሆን ያዳበረው የተፈተነ ባሕርይ ሲታይ ’ቅዱሳን ጽሑፎችን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት’ ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን ብቁ ነበር። ኢያሱ ሐሳብ የወለደው ምናባዊ ሰው ሳይሆን በሕይወት የነበረ የይሖዋ አገልጋይ ነበር። በግሪክኛው ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በስም ተጠቅሷል። (ሥራ 7:45፤ ዕብ. 4:8) ሙሴ በሕይወት ዘመኑ የተፈጸሙትን ክንውኖች እንዲጽፍ ከተደረገ የእርሱ ተተኪ የነበረው ኢያሱም በዓይኑ የተመለከታቸውን ነገሮች እንዲጽፍ መደረጉ ምክንያታዊ ነው። መጽሐፉን የጻፈው በወቅቱ የደረሱትን ክንውኖች የተመለከተ ሰው እንደሆነ ከኢያሱ 6:25 መመልከት ይቻላል። የአይሁድ ወግ መጽሐፉን የጻፈው ኢያሱ እንደሆነ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ መጽሐፉ ራሱ “ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ ”በማለት ይነግረናል።—ኢያሱ 24:26
4 ኢያሪኮ በጠፋችበት ወቅት ኢያሱ ከተማዋን መልሶ የሚገነባ እርጉም ይሁን በማለት ትንቢት የተናገረ ሲሆን ይህም 500 ዓመት አካባቢ ካለፈ በኋላ በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ዘመን አስደናቂ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ኢያሱ 6:26፤ 1 ነገ. 16:33, 34) ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በኢያሱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ክንውኖች በብዛት ጠቅሰው መጻፋቸው የኢያሱ መጽሐፍ ትክክለኛ ለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣል። መዝሙራዊው (በመዝ. 44:1-3፤ 78:54, 55፤ 105:42-45፤ 135:10-12፤ 136:17-22 ላይ)እነዚሁኑ በተደጋጋሚ ጠቅሶ የጻፈ ሲሆን ነህምያ (በነህ. 9:22-25 ላይ)፣ ኢሳይያስ (በኢሳ. 28:21 ላይ)፣ ሐዋርያው ጳውሎስ (በሥራ 13:19፤ በዕብ. 11:30, 31 ላይ) እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ (በያዕ. 2:25 ላይ)ጠቅሰው ጽፈዋል።
5 የኢያሱ መጽሐፍ እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ከገቡበት ከ1473 ከዘአበ አንስቶ ኢያሱ እስከ ሞተበት እስከ 1450 ከዘአበ ገደማ ድረስ ያለውን የ20 ዓመት ጊዜ የሚሸፍን ነው። “ይሖዋ አዳኝ ነው“ የሚል ትርጉም ያለው ኢያሱ (በዕብራይስጥ የሆሹዋ) የሚለው ስም እስራኤላውያን ድል አድርገው ምድሪቱን በተቆጣጠሩ ጊዜ ኢያሱ መሪ ሆኖ ከተጫወተው ሚና ጋር የሚስማማ ስም ነው። ላገኙት ድል ሙሉ በሙሉ ክብር ሊቀበል የሚገባው ይሖዋ እንዲሆን አድርጓል። በሴፕቱጀንት ውስጥ መጽሐፉ ኢየሱስ(የሆሹዋ ከሚለው ግሪክኛ ጋር አንድ ነው) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ኢየሱስ የሚለው ስም የተገኘውም ከዚሁ አጠራር ነው። ኢያሱ ባሳየው የድፍረት፣ የታዛዥነትና በአቋም የመጽናት ድንቅ ባሕርይ ’ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ’ ግሩም ትንቢታዊ ምሳሌ ይሆናል።—ሮሜ 5:1
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
21 ኢያሱ በታማኝነት የሚቀርብ አገልግሎትን በማስመልከት የተናገረውን ጥብቅ የስንብት ምክር በምታነብበት ጊዜ ስሜትህ አይነካም? “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን [“እናገለግላለን፣“ NW] በማለት ኢያሱ ከዛሬ 3,400 ዓመት በፊት የተናገራቸውን ቃላት አንተም አታስተጋባም? ወይም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ወይም ከሌሎች ታማኝ አገልጋዮች ተገልለህ ይሖዋን የምታገለግል ብትሆን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ጉዞ በጀመሩበት ወቅት ይሖዋ “ጽና፣ እጅግ በርታ“ በማለት ለኢያሱ የተናገራቸው ቃላት ማነቃቂያ አይሆኑልህም? ከሁሉም በላይ ደግሞ ’መንገድህ እንዲቀናልህ [መጽሐፍ ቅዱስን] በቀንም በሌሊትም አንብብ’ በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ብትከተል ከፍተኛ ጥቅም አያስገኝልህም? በእርግጥም፣ እንዲህ ያለውን ጥበብ ያዘለ ምክር የሚከተሉ ሁሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጥቅም ያገኛሉ።—24:15፤ 1:7-9
22 በኢያሱ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተመዝግበው የሚገኙት ክንውኖች እንዲሁ ጥንታዊ ታሪክ ብቻ አይደሉም። አምላካዊ መሠረታዊ ስርዓቶችን ጎላ አድርገው የሚገልጹ ሲሆን በተለይ የአምላክን በረከት ለማግኘት እምነትና ታዛዥነት ማሳየት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ” እንዲሁም “ጋለሞታይቱ ረዓብ . . . ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 11:30, 31) በተመሳሳይም ያዕቆብ፣ የእምነት ሥራዎችን በመሥራት ረገድ ረዓብ ለክርስቲያኖች ምሳሌ መሆኗን ጠቅሷል።—ያዕ. 2:24-26
23 ፀሐይና ጨረቃ ሳይንቀሳቀሱ ባሉበት ቦታ ስለ መቆማቸው የሚገልጸው በኢያሱ 10:10-14 ላይ የሚገኘው እንግዳ የሆኑ ክንውኖች ዘገባ እንዲሁም ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሲል ያደረጋቸው ሌሎች በርካታ ተአምራት ይሖዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክፉ ተቃዋሚዎቹ ላይ ጥፋት ለማምጣት ችሎታና ዓላማ ያለው መሆኑን የሚያስገነዝቡ ኃይለኛ ማሳሰቢያዎች ናቸው። ይሖዋ ይህን ጥፋት ለማምጣት በቁጣ እንደሚነሳ ለመግለጽ ኢሳይያስ በኢያሱም ሆነ በዳዊት ዘመን የፍልሚያ ቦታ የነበረችውን ገባኦንን በመጥቀስ “ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፣ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ”ሲል ተናግሯል። —ኢሳ. 28:21, 22
24 በኢያሱ መጽሐፍ ውስጥ የሠፈሩት ክንውኖች ስለ አምላክ መንግሥት የሚጠቁሙት ነገር ይኖር ይሆን? አዎን፣ አለ! የተስፋይቱን ምድር ነዋሪዎች ድል አድርገው በዚያ መስፈራቸው ከፍተኛ ብልጫ ካለው ነገር ጋር የተያያዘ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት አመልክቷል፦ “ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፣ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል።” (ዕብ. 4:1, 8, 9) “ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት” መግባታቸውን ለማጽናት ወደፊት ይገሰግሳሉ። (2 ጴጥ. 1:10, 11) ማቴዎስ 1:5 እንደሚያሳየው ረዓብ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅደመ አያት ሆናለች። በዚህ መንገድ የኢያሱ መጽሐፍ የመንግሥቱን ዘር ከሚዘረዝረው ዘገባ ጋር የተያያዘ ሌላ ወሳኝ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት የገባቸው ተስፋዎች በእርግጥ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ጠንካራ ማረጋገጫ ይሰጣል። ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ በኋላም የእነርሱ ዘር ለሆኑት ለእስራኤላውያን ስለተሰጠው የተስፋ ቃል ሲገልጽ የኢያሱን ዘመን በማስመልከት እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።” (ኢያሱ 21:45፤ ዘፍ. 13:14-17) በተመሳሳይም ጻድቅ የሆነውን የሰማይ መንግሥት በማስመልከት ይሖዋ የገባው ቃል “መልካም ነገር ሁሉ“ ፍጻሜውን ያገኛል!