የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ ጥምቀት፦ የጥምቀት እጩዎች ቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በተመደበላቸው ቦታ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ተጠማቂ ልከኛ ልብስና ፎጣ ይዞ መምጣት አለበት። ባለፉት ጊዜያት አንዳንዶች የለበሷቸው ልብሶች ተገቢ ያልሆኑና የተመልካቾችን ሐሳብ ወደ ሌላ የሚያዞሩ እንደሆኑ ተስተውሏል። የፖሊስተር ልብሶችን አለመጠቀሙ ይመረጣል። በተጨማሪም የጥምቀት እጩው ሊለብሰው የሚያስበው ልብስ ውኃ ሲነካው ሰውነትን የሚያሳይ ወይም ሰውነት ላይ የሚለጠፍ መሆን አለመሆኑን አስቀድሞ ማየት ጥሩ ይሆናል። ሽማግሌዎች አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች ከእጩ ተጠማቂዎች ጋር በሚከልሱበት ጊዜ እያንዳንዱ ተጠማቂ እነዚህን ነጥቦች የተገነዘበ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው ራሱን መወሰኑን የሚያሳይበት የጥምቀት እርምጃ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ የግል ጉዳይ ነው። ስለሆነም ለፎቶግራፍ ለመመቻቸት ሲባል መዘግየት አይገባም።
◼ ደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶች፦ እባካችሁ ስብሰባው በሚካሄድበት ከተማ በምትቆዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲሁም ወደ እዚያ ስትሄዱና ስትመለሱ ለ2000 የአውራጃ ስብሰባ የተዘጋጀውን ካርድ ደረታችሁ ላይ ለጥፉ። እንዲህ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። ደረት ላይ የሚለጠፉት ካርዶችና መያዣቸው በስብሰባው ላይ ስለማይገኙ በጉባኤያችሁ በኩል ማግኘት ይኖርባችኋል። ደረት ላይ የሚለጠፉትን ካርዶች ለእናንተና ለቤተሰቦቻችሁ ለመጠየቅ ስብሰባው የሚጀመርበት ቀን እስኪደርስ ድረስ አትጠብቁ። የወቅቱን በቅድሚያ የተሰጠ የሕክምና መመሪያ/የሕክምና ባለሙያዎችን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርግ ሰነድ መያዛችሁን አትርሱ።
◼ መስተንግዶ፦ የጉባኤ ጸሐፊዎች የማረፊያ ቦታ የሚፈልጉ ወንድሞችን ስም፣ ዕድሜና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች የያዙ ቅጾች ለአውራጃ ስብሰባው የመስተንግዶ ክፍል ወዲያውኑ መላካቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ያገኛችሁትን የማረፊያ ቦታ ለመተው ካሰባችሁ ወዲያውኑ ለአውራጃ ስብሰባው የመስተንግዶ ክፍል ማሳወቅ አለባችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ የመስተንግዶ ክፍሉ ማረፊያውን ለሌሎች ወንድሞች ለመመደብ ያስችለዋል።
◼ የፈቃደኝነት አገልግሎት፦ በስብሰባው ወቅት ከሚኖሩት የሥራ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ለማገልገል ጊዜ ልትመድቡ ትችላላችሁን? ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም እንኳ ወንድሞቻችሁን ማገልገላችሁ ትልቅ እገዛ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ እርካታ ያስገኝላችኋል። በዚህ ረገድ እርዳታ ማበርከት የምትችሉ ከሆነ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው ለፈቃደኛ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል አስታውቁ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ሊወስድ ከሚችል ሌላ ትልቅ ሰው ጋር በመሆን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
◼ የማስጠንቀቂያ ምክር፦ የመኪናዎቻችሁ በሮች ሁልጊዜ መቆለፋቸውንና መኪናውን ሰብሮ ለመዝረፍ የሚጋብዝ ከውጭ ሊታይ የሚችል ነገር ትታችሁ አለመሄዳችሁን አረጋግጡ። ሌቦችና ኪስ አውላቂዎች በብዛት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ዓይናቸውን ይጥላሉ። ውድ ዋጋ ያላቸውን ማናቸውንም ነገሮች መቀመጫችሁ ላይ ትታችሁ መሄዱ ጥበብ አይሆንም። ዙሪያችሁ ያለው ሁሉ ክርስቲያን ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አትችሉም። ሌሎች ለምን እንዲፈተኑ እናደርጋለን? ከውጭ የገቡ ሰዎች ልጆችን አባብለው ለመውሰድ ሙከራ እንዳደረጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ልጆቻችሁን በማንኛውም ጊዜ ከዓይናችሁ አታርቋቸው።