የይሖዋ በረከት ባለጸጎች ያደርገናል
1 ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው ስኬት የሚለካው በሚከፈለው ደሞዝ መጠን ነው። ለዚህ ነው ብዙዎች ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች ይበልጥ ደስታና እርካታ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸው። ይሁን እንጂ ገንዘብ ደስታን ሊገዛ ይችላል ብለው የሚያስቡ ሰዎች በጣም ተሳስተዋል። (መክ. 5:12) በቁሳዊ ነገሮች አንጻር ‘ባለጸጋዎች ለመሆን የቆረጡ’ ሰዎች ዘላቂ ደስታ የላቸውም። (1 ጢሞ. 6:9 NW ) በአንጻሩ ግን፣ የይሖዋ አገልጋዮች በእርግጥ ደስተኞችና ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ ባለጸጎች ናቸው። (ምሳሌ 10:22፤ ራእይ 2:9) እንዴት?
2 ባለጸጋ መሆናችንን የሚያሳዩ ነገሮች:- ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋልና የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ችሎታ አለን። ይሖዋ ዘላቂ ጥቅም እንድናገኝ ሲል በምድራዊ ድርጅቱ አማካኝነት ስለ ራሱና ስለ ልጁ ያለማቋረጥ ያስተምረናል። ትክክለኛ ማስተዋል ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብና የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ያስችለናል። (ያዕ. 4:8) ክፉና ደጉን መለየታችንና የአምላክን ሕግ መከተላችን ከአንዳንድ በሽታዎችና አደጋዎች ይጠብቀናል። ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚሰጠን ሙሉ ትምክህት አለን። ይህም አምላካዊ እርካታና የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል።—ማቴ. 6:33
3 የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በማፍራታችን ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር በሰላምና በአንድነት እንኖራለን። ጠንካራ ማሰሪያ በሆነው በፍቅር ስለተሳሰርን ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ አምላክም ሆነ ወንድሞቻችን ይተዉናል የሚል ስጋት ፈጽሞ አያድርብንም።—ገላ. 6:10
4 እውነተኛ ትርጉምና ዓላማ ያለው ሕይወት እየመራን ነው። በዓለም አቀፉ የምሥራች ስብከት ሥራ መካፈላችንን እንደ ታላቅ መብት እንቆጥረዋለን። ሌሎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱና ከእኛ ጋር በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ መርዳታችን ዘላቂ ደስታ ያስገኝልናል። በጣም ውድ የሆነው አገልግሎታችን ይሖዋን የሚያስከብረው ሲሆን እኛም ለስሙ ቅድስና የበኩላችንን አስተዋጽዖ በማድረጋችን እርካታ እናገኛለን። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለን ተስፋ በቅርቡ እውን እንደሚሆን ስለምናውቅ ብሩህ አመለካከት አለን።
5 አድናቆታችንን መግለጽ:- የይሖዋ በረከት በዚህች ምድር ላይ ከሰው ሁሉ ይበልጥ ባለጸጋ ስላደረገን ዘወትር አድናቂ እንሁን። (ምሳሌ 22:4) ስላገኘናቸው ነገሮች ለማሰላሰል በየዕለቱ ጊዜ የሚኖረን ከሆነ ይሖዋን ስለ ታላቅ ፍቅሩ ለማመስገንና ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ለመስጠት እንገፋፋለን።