የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 13—1 ዜና መዋዕል
ጸሐፊው፡- ዕዝራ
የተጻፈበት ቦታ፡- ኢየሩሳሌም (?)
ተጽፎ ያለቀው፡- 460 ከዘአበ አካባቢ
የሚሸፍነው ጊዜ፦ ከ1 ዜና መዋዕል 9:44 በኋላ:- 1077-1037 ከዘአበ
የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ እንዲሁ ድርቅ ያለ የዘር ሐረግ ዝርዝር ወይም የሳሙኤልና የነገሥት መጻሕፍትን ሐሳብ ብቻ የሚደግም መጽሐፍ ነውን? በፍጹም አይደለም! ከዚያ ይልቅ እውቀት የሚጨምርና ወሳኝ የሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ነው። በተጻፈበት ዘመን ብሔሩንና ብሔሩ የሚያቀርበውን አምልኮ እንደገና ለማደራጀት ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ሁሉ ከተጻፈበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ለአምላክ የሚቀርበው አምልኮ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ የሚጠቁም በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ዘገባ የያዘ መጽሐፍ ነው። የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እጅግ ውብ በሆነ መንገድ ለይሖዋ የቀረቡትን የውዳሴ መግለጫዎች የያዘ መጽሐፍ ነው። ጽድቅ ስለሰፈነበት የይሖዋ መንግሥት ድንቅ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን በዚህ መንግሥት ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ በማንበባቸው የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ነው። ሁለቱ የዜና መዋዕል መጻሕፍት በአይሁዳውያንም ሆነ በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የኖሩ መጻሕፍት ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚው ጄሮም ለአንደኛና ለሁለተኛ ዜና መዋዕል መጻሕፍት ከነበረው እጅግ ከፍ ያለ ግምት የተነሣ “የብሉይ ኪዳን ዓይነተኛ መጻሕፍት” እንደሆኑ አድርጎ የተመለከታቸው ሲሆን “ካላቸው ጉልህ ቦታ አንጻር ቅዱሳን ጽሑፎችን አውቃለሁ የሚል ማንኛውም ሰው እነዚህን መጻሕፍት የማያውቅ ከሆነ ራሱን ያታልላል” ሲል ተናግሯል።
2 ሁለቱ የዜና መዋዕል መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ አንድ መጽሐፍ ወይም ጥቅልል የነበሩና ከጊዜ በኋላ ግን አመቺ እንዲሆኑ ሲባል ለሁለት የተከፈሉ ይመስላል። የዜና መዋዕል መጽሐፍ የተጻፈበት ምክንያት ምንድን ነው? በወቅቱ የነበረው መቼት ምን እንደሚመስል ተመልከት። የባቢሎኑ ግዞት ካበቃ ወደ 77 ዓመታት አልፈዋል። አይሁዳውያንም ተመልሰው በምድራቸው ላይ ሰፍረዋል። ይሁን እንጂ እንደገና በተገነባው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከሚከናወነው የይሖዋ አምልኮ የመራቅ አደገኛ አዝማሚያ ይታይ ነበር። የፋርስ ንጉሥ መሳፍንትንና የአምላክን ሕግ (እንዲሁም የንጉሡን ሕግ) የሚያስተምሩ ሰዎችን እንዲሾምና የይሖዋን ቤት እንዲያስውብ ለዕዝራ ሥልጣን ሰጥቶት ነበር። በክህነት የሚያገለግሉት መብቱ ያላቸው ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ለመከታተልና ለክህነቱ አገልግሎት የድጋፍ ምንጭ የነበረውን የነገዶቹን ውርሻ በትክክል ለማረጋገጥ ትክክለኛ የዘር ሐረግ ዝርዝር መገኘቱ አስፈላጊ ነበር። ይሖዋ መንግሥቱን በሚመለከት ከተናገረው ትንቢት አንጻርም ቢሆን ስለ ይሁዳ ነገድና ስለ ዳዊት የዘር ሐረግ ግልጽና አስተማማኝ መረጃ ተመዝግቦ መገኘቱ በጣም አስፈላጊ ነበር።
3 ዕዝራ፣ አይሁዳውያኑ ከያዛቸው የግዴለሽነት አዚም ተላቅቀው በቃል ኪዳን የታሠረውን የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ያገኙ ሰዎች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም በዜና መዋዕል መጻሕፍት ውስጥ የብሔሩን ሙሉ ታሪክ እንዲሁም የሰውን ዘር አመጣጥ ወደ ኋላ እስከ መጀመሪያው ሰው እስከ አዳም ድረስ ተመልሶ በዝርዝር አስቀምጦላቸዋል። ዋናው ትኩረቱ የዳዊት መንግሥት ስለነበር ፈውስ የማይገኝለትን የአሥሩን ነገድ መንግሥት ታሪክ ጨርሶ በመተው የይሁዳን ታሪክ ብቻ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ታላላቆቹ የይሁዳ ነገሥታት ቤተ መቅደሱን በመገንባትና በማደስ ሥራ እንደተካፈሉ እንዲሁም ለአምላክ በሚቀርበው አምልኮ በግንባር ቀደምትነት በቅንዓት እንደተሳተፉ ገልጿል። አምላክ ተመልሰው እንደሚቋቋሙ የሰጠውን ተስፋ ጎላ አድርጎ ቢገልጽም መንግሥቱ እንዲገለበጥ ምክንያት ስለሆነው ሃይማኖታዊ ኃጢአትም ሳይጠቅስ አላለፈም። ከቤተ መቅደሱ፣ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመዘምራኑና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በማተኮር የንጹሕ አምልኮ አስፈላጊነት ጎላ ብሎ እንዲታይ አድርጓል። እስራኤላውያኑ ከግዞት በተመለሱበት ምክንያት ማለትም በኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኮ መልሶ በመቋቋሙ ላይ ያተኮረ ታሪካዊ ዘገባ በማግኘታቸው ተበረታትተው መሆን አለበት።
4 ዕዝራ የዜና መዋዕል መጻሕፍትን እንደጻፈ የሚያረጋግጠው ማስረጃ ምንድን ነው? የሁለተኛ ዜና መዋዕል የመጨረሻ ሁለት ቁጥሮች ማለትም 36:22, 23 ከዕዝራ የመክፈቻ ቁጥሮች ማለትም ከዕዝራ 1:1, 2 ጋር የሚመሳሰሉ ሲሆን በሁለተኛ ዜና መጨረሻ ላይ ያለው ሐሳብ የሚቋጨው በዕዝራ 1:3 ላይ ነው። በመሆኑም የዜና መዋዕል መጻሕፍትን የጻፈው የመጽሐፈ ዕዝራ ጸሐፊ መሆን አለበት። በዜና መዋዕል መጻሕፍትና በዕዝራ መካከል ያለው የአጻጻፍ ስልት፣ የቋንቋ፣ የቃላትና የፊደል ተመሳሳይነትም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ መግለጫዎች በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አይገኙም። የዕዝራን መጽሐፍ የጻፈው ዕዝራ የዜና መዋዕል መጻሕፍትንም ጽፎ መሆን አለበት። የአይሁዳውያንም አፈ ታሪክ ይህንኑ ማጠቃለያ የሚደግፍ ነው።
5 ይህን እውነተኛና ትክክለኛ ታሪክ ለማጠናቀር ከዕዝራ የተሻለ ብቃት ያለው ሰው አልነበረም። “ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) ይሖዋም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እገዛ አድርጎለታል። ፋርሳዊው የዓለም ገዥ በዕዝራ ላይ የተንጸባረቀውን የአምላክ ጥበብ በማስተዋል በይሁዳ አውራጃ ከፍተኛ የሕዝብ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ዕዝራ 7:12-26) በዚህ መንገድ ከአምላክና ከንጉሡ ሥልጣን የተቀበለው ዕዝራ በጊዜው የነበሩትን ምርጥ መዛግብት በመጠቀም ዘገባውን ማጠናቀር ችሏል።
6 ዕዝራ ከፍተኛ ምርምር አካሂዷል። በየዘመናቱ የነበሩ የታመኑ ነቢያት እንዲሁም ሕጋዊ መዛግብትን የሚያዘጋጁና የሚያስቀምጡ ኦፊሴላዊ ዘጋቢዎች ያጠናቀሯቸውን ጥንታዊ የአይሁድ ታሪክ መዛግብት አገላብጧል። ካገላበጣቸው መዛግብት መካከል አንዳንዶቹ በእስራኤልና በይሁዳ መንግሥታት እጅ የሚገኙ መዛግብት፣ የዘር ሐረግ ዝርዝሮች፣ በነቢያት የተጻፉ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ሥራዎችና በነገድ ወይም በቤተሰብ አለቆች እጅ የሚገኙ መዛግብት ሊሆኑ ይችላሉ። ዕዝራ ቢያንስ ወደ 20 የሚያህሉ እንዲህ የመሰሉ ምንጮችን ጠቅሷል። ዕዝራ እነዚህን ምንጮች በግልጽ መጥቀሱ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ፍላጎቱ ካላቸው ከምንጮቹ ማረጋገጥ እንደሚችሉ በሐቀኝነት መናገሩ ነበር። ይህም ቃሉ ትክክለኛና እውነተኛ ነው የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ሚዛን እንዲደፋ የሚያደርግ ነው። በዕዝራ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን በዜና መዋዕል መጻሕፍት ላይ እምነት እንዲጥሉ ካደረጓቸው ምክንያቶች በመነሳት ዛሬም እኛ ስለ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ትክክለኝነት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
7 ዕዝራ ‘ከባቢሎን የወጣው’ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ ሎንጊማነስ ሰባተኛ የግዛት ዘመን ማለትም በ468 ከዘአበ ስለሆነና በ455 ከዘአበ ነህምያ ወደዚያ ስለመምጣቱ ምንም የጠቀሰው ነገር ባለመኖሩ የዜና መዋዕል መጽሐፍ የተጠናቀቀው በእነዚህ ዓመታት መካከል ምናልባትም በ460 ከዘአበ ገደማ በኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም። (ዕዝራ 7:1-7፤ ነህምያ 2:1-18) በዕዝራ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የዜና መዋዕል መጻሕፍት ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትና ጠቃሚ የሆኑት ቅዱሳን ጽሑፎች’ እውነተኛ ክፍል እንደሆኑ አድርገው ተቀብለዋቸዋል። ዲቭሬህ ሄያሚም ብለው ይጠሯቸው የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “የዘመኑ ሁኔታ” ወይም የጊዜው ታሪክ ማለት ነው። ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ የግሪክ ሰፕቱጀንት ተርጓሚዎች የዜና መዋዕል መጻሕፍት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆናቸውን ተቀብለው አካትተዋቸዋል። መጽሐፉን ለሁለት የከፈሉት ሲሆን ለሳሙኤልና ለነገሥት መጽሐፍ ወይም ለጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ማሟያ እንደሚሆን በማሰብ ፓራሊፖሜኖን የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ትርጉሙም “የታለፉ ነገሮች (ሳይነገር የቀረ፣ የተዘለለ)” የሚል ነው። ምንም እንኳ ስሙ ፍጹም ተስማሚ ነው ባይባልም ይህን ማድረጋቸው በራሱ የዜና መዋዕል መጽሐፍ ትክክለኛና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን አምነው እንደተቀበሉ የሚያሳይ ነው። ጄሮም የላቲኑን ቩልጌት ትርጉም ባዘጋጀበት ጊዜ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “የአጠቃላዩ መለኮታዊ ታሪክ ክሮኒኮን ብለን ብንጠራቸው ይበልጥ ትርጉም አዘል ይሆናል።” “ዜና መዋዕል” (በእንግሊዝኛ ክሮኒክልስ) የሚለው ስያሜ የተገኘው ከዚህ ይመስላል። ዜና መዋዕል ነገሮች የተፈጸሙበትን ቅደም ተከተል ጠብቆ የቀረበ ዘገባ ማለት ነው። የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ የዘር ሐረግ ዝርዝሩን ካሰፈረ በኋላ ዋና ትኩረቱን ያደረገው ከ1077 ከዘአበ አንስቶ እስከ ንጉሡ ሞት ድረስ ባለው የንጉሥ ዳዊት ዘመን ላይ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
22 በዕዝራ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ከዚህ መጽሐፍ ብዙ ጥቅም አግኝተዋል። በጊዜው የነበረውና አዎንታዊው አመለካከት በትክክል የተንጸባረቀበትን ይህንን ወጥ የሆነ ታሪክ በማግኘታቸው ይሖዋ ከንጉሥ ዳዊት ጋር ለገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን ካለው ታማኝነት የተነሳ እንዲሁም ለስሙ ሲል ያሳያቸውን ምህረት ማድነቅ ችለዋል። ባገኙት ማበረታቻ ተነሣስተው ንጹሑን የይሖዋ አምልኮ በአዲስ መልክ በቅንዓት ማከናወን ችለዋል። የዘር ሐረግ ዝርዝሩ እንደገና በተገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ በነበራቸው ካህናት ላይ ትምክህታቸውን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል።
23 የአንደኛ ዜና መጽሐፍ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም ትልቅ ጥቅም ነበረው። ማቴዎስና ሉቃስ ከዘር ሐረጉ ዝርዝር በመጥቀስ ኢየሱስ ክርስቶስ “የዳዊት ልጅ” እና ትክክለኛ መብት ያለው መሲሕ መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ ችለዋል። (ማቴዎስ 1:1–16፤ ሉቃስ 3:23-38) እስጢፋኖስ የመጨረሻ ምሥክርነቱን ሲደመድም ዳዊት የይሖዋን ቤት ለመገንባት ስላቀረበው ጥያቄና ሰሎሞን ግንባታውን ስለማከናወኑ ጠቅሷል። ከዚያም ‘ልዑሉ የሰው እጆች በሠሩት ቤት እንደማይኖር’ በመግለጽ በሰሎሞን ዘመን የተሠራው ቤተ መቅደስ የበለጠ ክብር ያለውን ሰማያዊ ነገር እንደሚያመለክት ጠቁሟል።—ሥራ 7:45-50
24 ዛሬ ስላሉት እውነተኛ ክርስቲያኖችስ ምን ለማለት ይቻላል? የአንደኛ ዜና መጽሐፍ እምነታችንን ሊገነባልንና ሊያነቃቃን ይገባል። ቅንዓት ከተንጸባረቀበት የዳዊት ምሳሌ ብዙ ልንኮርጀው የምንችለው ነገር አለ። ዳዊት አዘውትሮ የይሖዋን መመሪያ የሚጠይቅ ሰው በመሆኑ የታመነ ሳይሆን ከቀረው ከሳውል ምንኛ የተለየ ነበር! (1 ዜና 10:13, 14፤ 14:13, 14፤ 17:16፤ 22:17-19) ዳዊት የይሖዋን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ከማምጣቱ፣ ለይሖዋ ካቀረባቸው የውዳሴ መዝሙሮች፣ ሌዋውያኑን ለአገልግሎት ከማደራጀቱና ክብራማ ቤት ለይሖዋ ለመገንባት ከመጠየቁ አንጻር ሲታይ ዳዊት ለይሖዋና ለይሖዋ አምልኮ አንደኛ ቦታ ይሰጥ እንደነበር መረዳት ይቻላል። (16:23-29) የሚያማርር ሰውም አልነበረም። ለራሱ ልዩ መብት የሚፈልግ ሳይሆን የይሖዋን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ የሚጥር ሰው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ልጁ እንዲያከናውነው ባደረገበት ጊዜ ዳዊት ከእርሱ ሞት በኋላ የሚጀመረውን ሥራ ለማደራጀት ሲል በሙሉ ልቡ ለልጁ መመሪያ አልፎ ተርፎም ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ሀብቱንም ከመስጠት ወደኋላ አላለም። (29:3, 9) በእርግጥም ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው!—ዕብ. 11:32
25 ከዚያ ደግሞ የላቀው የመደምደሚያ ሐሳብ የሚገኝባቸው የመጨረሻ ምዕራፎች አሉ። ዳዊት ይሖዋን ያወደሰበትና ‘ክቡር ስሙን’ ያከበረበት ግሩም መግለጫ በዘመናችን የይሖዋንና በክርስቶስ የሚመራውን የመንግሥቱን ክብር ለማሳወቅ ያለንን መብት በደስታ እንድንቀበል ሊያነሳሳን ይገባል። (1 ዜና 29:10-13) ለይሖዋ ዘላለማዊ መንግሥት ያለንን አድናቆት ራሳችንን ለአገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በማቅረብ በምንገልጽበት ጊዜ እምነታችንና ደስታችን የዳዊትን የመሰለ እንዲሆን ምኞታችን ነው። (17:16-27) በእርግጥም የአንደኛ ዜና መጽሐፍ በዘሩ አማካኝነት ስለሚተዳደረው የይሖዋ አምላክ መንግሥት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ይበልጥ ጉልህ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርግ ሲሆን ስለ ይሖዋ አምላክ ዓላማ የሚገለጡትን ተጨማሪ ድንቅ ነገሮች በጉጉት እንድንጠባበቅም ያደርገናል።