አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች
1 በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እያደገ ሲሄድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ስለመሥራት ለማሰብ የምንገደድበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። አንዳንድ አዳራሾች አሁንም ተሰብሳቢው ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ የተወሰኑት ውጭ ይቀመጣሉ። ይህ ሁኔታ የወደፊቱን ጭማሪ ግምት ውስጥ ያላስገባ ዕቅድ በማውጣት ጠባብ የመንግሥት አዳራሽ ሠርተን አዳራሹ ገና ከመሠራቱ ጠባብ ሆኖ እንዳይገኝ ጥንቃቄ የማድረጉን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የወደፊቱን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ወደ መጨረሻው ዘመን ጠልቀን እንደገባንና ‘ታላቁ መከራ’ በጣም እንደቀረበ ብናውቅም የመንግሥት አዳራሾች ለመገንባት እቅድ መንደፋችን የተገባ ነው። አንዳንድ ጉባኤዎች መከራየቱን ይበልጥ አመቺ ሆኖ ያገኙት ይሆናል። በአብዛኛው ግን ጉባኤዎች ቦታ ገዝተው ተስማሚ የመንግሥት አዳራሽ መገንባቱን ይበልጥ የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል።
2 ይህን እቅድ የመንደፍ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው? ሁሉም ሽማግሌዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይገባል። አዲስ የመንግሥት አዳራሽ መገንባት ሲያስፈልግ ሽማግሌዎች ወይም እነርሱ የወከሏቸው ወንድሞች ግንባር ቀደም ሆነው አዳራሽ መሥሪያ ቦታ የሚያፈላልጉ ቢሆንም ሁሉም አማራጭ የሚሆኑ ቦታዎችን መፈለግ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ምቹ ቦታ በስጦታ መልክ ወይም በግዥ ይገኝ ይሆናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ጉባኤዎች ቤት ገዝተው ለጉባኤው በሚያመች መንገድ አድሰው መጠቀሙን ተስማሚ ሆኖ አግኝተውታል። ይሁን እንጂ ቦታውን በተመለከተ ከማኅበሩ የጽሑፍ ፈቃድ ከማግኘታችሁ በፊት በማንኛውም መንገድ ራሳችሁንም ሆነ ማኅበሩን ግዴታ ውስጥ አታስገቡ። እንዲህ ያለው የመንግሥት አዳራሽ ማስፋፊያ እቅድ በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር በሚገኘው በአዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዴስክ ቀጥተኛ ድጋፍ የሚከናወን ነው።
አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታና ገንዘብ አሰባሰብ
3 ጉባኤው የራሱን የመንግሥት አዳራሽ ስለሚያገኝበት ሁኔታ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ በግላችሁ ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ መለገስ ወይም ለጊዜው የማትጠቀሙበት ገንዘብ ካለ በብድር መልክ መስጠት ትችሉ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ከይሖዋ በረከት ጋር በየወሩ በቋሚነት ምን ያክል አስተዋጽዖ ማድረግ እንደምትችሉ ለመወሰን ትፈልጉ ይሆናል። ይህ ሙሉ በሙሉ በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ነገር ቢሆንም ሽማግሌዎች አስቀድመው እቅድ ለማውጣት ይረዳቸው ዘንድ ሁሉም በአንድ ጊዜ ምን ያህል ገንዘብ በስጦታ መለገስ ወይም ማበደር አሊያም በየወሩ ምን ያህል ማዋጣት እንደሚችል ስሙን ሳይጽፍ የገንዘቡን መጠን ብቻ በወረቀት ላይ አስፍሮ እንዲሰጥ ጉባኤውን ይጠይቁ ይሆናል። አብዛኛዎቹ ጉባኤዎች ከጉባኤው ሊገኝ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ካወቁ በኋላ ከማኅበሩ ተጨማሪ ብድር መጠየቁን አስፈላጊ ሆኖ ያገኙታል። እንደዚያ ማድረግ የሚያስፈልግ ከሆነ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዴስክ አስፈላጊውን ከወረቀት ጋር የተያያዘ ሥራ እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል።
4 ሽማግሌዎቹ የግንባታ ሥራውን የሚከታተል የጉባኤ የግንባታ ኮሚቴ ያቋቁማሉ። ከተቻለ የግንባታና የንግድ ተሞክሮ ያላቸውን ወንድሞች በኮሚቴው ውስጥ ማካተት ጥሩ ይሆናል። ኮሚቴው ሥራውን የሚያከናውነው የማኅበሩ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ዴስክ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ነው። በድምፀ ውሳኔ ጸድቀው በጽሑፍ በሰፈሩ ውሳኔዎች ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ማድረግ አይኖርበትም።
5 የግንባታ ሥራው ሲጀምር ሁላችንም በፈቃደኝነት መርዳት እንችላለን። የአናጺነት፣ የግንበኝነት፣ የቧንቧ ሥራ ወይም ሌላ ዓይነት ሙያ አለህን? ከሆነ ለሥራው ከፍተኛ ድርሻ ልታበረክት ትችል ይሆናል። ሆኖም በፈቃደኝነት ለመሥራት የግድ ባለሙያ መሆን አለብህ ማለት አይደለም። ቦታውን ለግንባታ ማዘጋጀት፣ የግንባታ ዕቃዎችን ማቅረብ፣ አንዳንድ ነገሮችን መግጠም፣ ማፅዳትና የመሳሰሉ ሌሎች ሥራዎችም ይኖራሉ። እህቶች በአንዳንድ የግንባታ ሥራዎች መካፈልና ለሠራተኞች ምግብ በማብሰል መርዳት ይችላሉ። በምድረ በዳ ለተሠራው መገናኛ ድንኳንም ሆነ ሰሎሞን ላስገነባው ቤተ መቅደስ ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል ጥሩ የእጅ ሞያ ያላቸው ሰዎች እንዲሠሩ እንደተደረገ ሁሉ በጉባኤውም ሆነ በአጎራባች ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ጥረት በጥሩ ሁኔታ አስተባብሮ መጠቀም ይቻላል።—ዘጸ. 35:34, 35፤ 2 ዜና 2:11-16
6 የግንባታ ሥራው ሳያስፈልግ ተጓትቶ የስብከት ተልእኳችንን የምንወጣበትን ጊዜ እንዳይሻማብን የመንግሥት አዳራሹ በተቻለ መጠን ቶሎ መጠናቀቅ ይኖርበታል። የሽማግሌዎች አካል በመስክ አገልግሎት ዘወትር ለመካፈል የሚያስችል የማያሻማ ፕሮግራም ማውጣት አለበት። በግንባታ ሥራው ላይ እምብዛም ተሳትፎ ማድረግ የማይችሉ አስፋፊዎች ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ማድረግ ይችሉ ይሆናል። አንድ ሰው በግንባታ ሥራው ብዙ ጊዜውን ከማጥፋቱ የተነሳ አስፈላጊ የሆኑ የቤተሰብ ጉዳዮችን ችላ እንዳይል ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በፕሮግራም መመራት የግንባታ ሥራውን፣ የቤተሰብ ጥናትን፣ የጉባኤ ስብሰባዎችንና የመስክ አገልግሎትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጎን ለጎን ለማስኬድ ይረዳል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ አንዳንድ ጊዜ ረጅም ሰዓት ከባድ ሥራ መሥራት ሊጠይቅ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ በሙሉ ልብ የሚያገለግሉትን ይባርካል።—ቆላ. 3:23, 24
7 የመንግሥት አዳራሹን በመገንባቱ ሂደት ላይ የመንፈስ ፍሬዎችን በተለይ ደግሞ ፍቅርን፣ ትዕግሥትን፣ የዋህነትንና ራስን መግዛትን ማሳየት አስፈላጊ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። (ገላ. 5:22, 23) ብዙውን ጊዜ አንድ ሥራ እናንተ በፈለጋችሁት መንገድ ያልተሠራበት በቂ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህን ከግምት ውስጥ ማስገባትና አንድ ነገር በተለያዩ መንገዶች ሊሠራ እንደሚችል ማስታወሱ ሁላችንም ሥራውን በበላይነት ለመከታተል ከተሾሙ ወንድሞች ጋር ለመተባበር ይረዳል። በግንባታ ሂደት ወቅት የሚደረግ የተንዛዛ ውይይት ወይም በግል ምርጫ ላይ ብቻ የተመሠረተ ጭቅጭቅ ጊዜ ከማባከኑና ሥራውን ከማጓተቱ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በግንባታ ሥራ ለተሰማሩ ወንድሞች ስኬት ቁልፍ ሆኖ የተገኘው ሰላም በመካከላችሁ እንዳይኖር እንቅፋት ይሆናል።—መዝ. 133:1፤ ያዕ. 3:17
8 ግንባታው ሲጠናቀቅ ሕንፃው ለአምላክ አገልግሎት የሚወሰንበትን ፕሮግራም ማዘጋጀት የተገባ ይሆናል። ቅርንጫፍ ቢሮው ንግግሩን የሚያቀርብ ወንድም የሚመድብ ሲሆን ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወንበትን ቀን ይወስናል። አንዳንድ ጉባኤዎች በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች አዲሱን አዳራሽ እንዲያዩ “ለጉብኝት ክፍት” የሚቆይባቸው ጥቂት ሰዓታት ጊዜ ይመድባሉ። ብዙውን ጊዜ ከውሰናው ንግግር በፊት የመንግሥት አዳራሹ ሲገነባ ያጋጠሙ ተሞክሮዎችንና የጉባኤው ታሪክ ይቀርባል። ፕሮግራሙ ቅዳሜ የሚውል ከሆነ እሑድ ልዩ የሕዝብ ንግግርና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ማድረግ ይቻላል።
የመንግሥት አዳራሹ አገልግሎት
9 ብዙ ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሽ ማግኘታቸው በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ረገድ የታየ አንድ አስደሳች እድገት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት አዳራሹ የማን ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ የትኛውም ጉባኤ ቢሆን የመንግሥት አዳራሹ “ባለቤት” እንደሆነ ሊሰማው አይገባም። አዳራሹ ለይሖዋ አምልኮ የተወሰነ ነው። አዳራሹን የሠሩት ወይም የተከራዩት ጉባኤዎች በአደራ እንደተሰጣቸው አድርገው ሊያዩት ይችላሉ። የሽማግሌዎች አካላት የመንግሥት አዳራሹ የመንግሥቱን ጥቅሞች በሚያስጠብቅ መንገድ በአግባቡ አገልግሎት መስጠቱን የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው። የሽማግሌዎች አካላት አዳራሹ ዕለት ተዕለት የሚሰጠውን አገልግሎትና የሚደረግለትን ጥገና የሚከታተሉ አስተዋይ ሽማግሌዎችን ያካተተ ኮሚቴ ያቋቁማሉ።
10 የመንግሥት አዳራሹ አንድ ላይ እንድንሰበሰብ ከሚያስችሉን የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅቶች መካከል አንዱ ነው። ስለሆነም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ከልብ መደገፍና ለመንግሥት አዳራሾቻችን ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ አመስጋኝነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። ንጉሥ ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 122:1) እንግዲያው ሁላችንም ዳዊትና ጥንት የነበሩ ሌሎች የታመኑ አገልጋዮች ለይሖዋ እውነተኛ አምልኮ የተወሰኑ ሕንፃዎችን ግንባታና አጠቃቀም በተመለከተ የተዉልንን ምሳሌ እንኮርጅ።