የመታሰቢያውን በዓል የሚመለከቱ ማሳሰቢያዎች
በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው እሁድ ሚያዝያ 8 ነው። ሽማግሌዎች ለሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጡ ይገባቸዋል:-
◼ ስብሰባው የሚደረግበትን ሰዓት ስትወስኑ ቂጣውና ወይኑ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መዞር እንደሌለባቸው አስታውሱ። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሚያዝያ 27, 1998 ለሽማግሌዎች የተላከውን ደብዳቤ ተመልከቱ።
◼ ተናጋሪውን ጨምሮ ሁሉም ተሰብሳቢዎች በዓሉ የሚከበርበት ትክክለኛ ሰዓትና ቦታ ሊነገራቸው ይገባል።
◼ ተገቢው ዓይነት ቂጣና ወይን ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት።—መጠበቂያ ግንብ 2-106 ገጽ 17ን ተመልከቱ።
◼ ሳህኖች፣ ብርጭቆዎች እንዲሁም ተስማሚ የሆነ ጠረጴዛና የጠረጴዛ ልብስ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጥተው ቀደም ብሎ በየቦታቸው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።
◼ የመንግሥት አዳራሹም ሆነ ሌላ የመሰብሰቢያ ቦታ ቀደም ብሎ በሚገባ መጽዳት አለበት።
◼ አስተናጋጆች እንዲሁም ቂጣውንና ወይኑን የሚያዞሩ ወንድሞች ቀደም ብሎ ሊመረጡና ተገቢ ስለሆነው አሠራርና ስለ ሥራ ድርሻቸው መመሪያ ሊሰጣቸው ይገባል። ለሽማግሌዎች በሙሉ ከተላከው ከሚያዝያ 27, 1998 ደብዳቤ ላይ “የምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን አቀራረብና አስተላለፍ እንዴት መሆን ይገባዋል?” የሚለውን አብራችሁ ከልሱ።
◼ አቅመ ደካማ የሆኑ እንዲሁም በቦታው መገኘት የማይችሉ ቅቡዓን መካፈል የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል።
◼ እያንዳንዱ ጉባኤ ራሱን ችሎ የመታሰቢያውን በዓል ቢያከብር ይመረጣል። በዓሉን በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ለማክበር ፕሮግራም ተይዞ ከሆነ በመተላለፊያዎች ወይም በመግቢያው አካባቢ እንዲሁም ሕዝብ በሚጠቀምባቸው የእግረኛ መንገዶችና በመኪና ማቆሚያ አካባቢ ጭንቅንቅ እንዳይፈጠር በጉባኤዎቹ መካከል ጥሩ ቅንጅት ሊኖር ይገባል።