በአገልግሎት ክልላችሁ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመፈለግ ረገድ ንቁ ሁኑ
1 ይሖዋ “ና . . . የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚል ጥሪ አቅርቧል። (ራእይ 22:17) ለዚህ ጥሪ ምላሽ ከሚሰጡት መካከል ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይገኙበታል። በዚህ ምክንያት በተለያዩ አገሮች ውስጥ ብዙ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና ቡድኖች ተቋቁመዋል።
2 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና ቡድኖች የሚያደርጉት የስብከት እንቅስቃሴ በሙሉ የሚያተኩረው በአገልግሎት ክልሎቻቸው ውስጥ የሚገኙ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በማግኘት ላይ ቢሆንም በአገራችን እስከ አሁን ያልተመሰከረላቸው ብዙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሉ።
3 እንዴት መርዳት ትችላላችሁ? ሰዎች በሚዘዋወሩባቸው ቦታዎች የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ አይታችኋል? በምትሠሩበት ቦታ ወይም በትምህርት ቤት መስማት የተሳነው የቤተሰብ አባል ያለው ሰው ታውቃላችሁ? የዕለት ተዕለት ሥራዎቻችሁን ስታከናውኑ በዚያው መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመፈለግ ንቁ ሁኑ። ሆኖም የመንግሥቱ ምሥክርነት እንዲደርሳቸው እንዴት ልትረዷቸው ትችላላችሁ?
4 ምሥክርነት መስጠት:- መስማት የተሳነው ሰው ስታገኙ አድራሻውን በጉባኤያችሁ ጸሐፊ በኩል ለቅርንጫፍ ቢሮው መላክ ይኖርባችኋል። ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ያለው የምልክት ቋንቋ ቡድን ሰውዬውን ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግ አድራሻው ይላክለታል።
5 በአካባቢያችሁ የሚገኙትን መስማት የተሳናቸው ሰዎች በመንፈሳዊ መርዳት የሚችል ሰው በአቅራቢያችሁ ባይኖርስ? እንዴት መርዳት ትችላላችሁ? ተመልሳችሁ በመሄድ መስማት ከሚችሉት የቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱን ለምን አታነጋግሩም? መስማት የተሳነውን ግለሰብ ፍላጎት ለመቀስቀስ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀ ቪዲዮ ልታሳዩት እንደምትችሉ ግለጹ። አንዳንድ አስፋፊዎች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማነጋገር ሲሉ የምልክት ቋንቋ ተምረዋል። (ሥራ 16:9, 10) አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹርና እውቀት መጽሐፍን በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በቪዲዮ ማግኘት ይቻላል። ጥቂት የቪዲዮ ካሴቶች በእጃችን አሉ። በእነዚህ መሣሪያዎች ተጠቅሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት እስከ አሁን ብዙ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል።
6 በምትኖሩበት አካባቢ ያሉ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመፈለግ ረገድ ንቁ በመሆን የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ።—ማቴ. 10:11፤ ራእይ 7:9