‘መልካም ሥራ መሥራታችሁን’ ቀጥሉ
1 የይሖዋ አምላክ አገልጋይ ስትሆኑ አንድ መልካም ሥራ ሠርታችኋል። ይሁን እንጂ አሁን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ተፈታታኝ የሆነው ነገር ‘መልካም ሥራ በመሥራት’ መቀጠሉ ነው። (ገላ. 6:9) ምንም እንኳ ይህ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ልታደርጉት ትችላላችሁ። እንዴት?
2 የኢየሱስን ዓይነት አስተሳሰብ አዳብሩ:- እናንተም በመንግሥቱ ተስፋ ላይ የምታተኩሩ ከሆነ ፈተና ሲያጋጥማችሁ እንደ ኢየሱስ መጽናት ትችላላችሁ። (ዕብ. 12:2, 3) ይሖዋ እንደሚወድዳችሁና ስኬታማ እንድትሆኑ እንደሚፈልግ እርግጠኞች ሁኑ። (2 ጴጥ. 3:9) እንደሚረዳችሁ በመተማመን ትምክህታችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ። (1 ቆሮ. 10:13) ይሖዋ እንድትጸኑ ይረዳችሁ ዘንድ በመለመን በጸሎት ጽኑ። (ሮሜ 12:12) የምታሳዩት ጽናት በአምላክ ፊት ሞገስ እንደሚያስገኝ ባላችሁ የጸና እምነት ደስ ይበላችሁ። (ሮሜ 5:3-5) ‘የክርስቶስ ኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ’ በማዳበር የምታሳዩት ታማኝነት የግል እርካታ የሚያስገኝላችሁ ሲሆን የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል።—ሮሜ 15:5፤ ምሳሌ 27:11
3 ትክክለኛውን ነገር ማድረጋችሁን ቀጥሉ:- ይሖዋ ሕዝቦቹ መልካም የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀሙ። በግል የአምላክን ቃል የማንበብ እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያዘጋጃቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች የማጥናት ጥሩ ልማድ አዳብሩ። ለሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀት፣ በስብሰባዎቹ ላይ በመገኘትና በመሳተፍ ረገድ ታማኞች ሁኑ። ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር ተጫወቱ። በመስክ አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ የማድረግና ምሥራቹን ለሌሎች በማድረስ ረገድ ችሎታችሁን የማሻሻል ሊደረስበት የሚችል ግብ አውጡ።
4 መልካም ሥራ መሥራታችሁን ልትቀጥሉና በአጸፋውም ታላቅ ደስታ ልታገኙ የምትችሉት በዚህ መንገድ ነው። በዚህ ረገድ በኢጣሊያ የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋን ሳገለግል ውዬ አመሻሹ ላይ ወደ ቤቴ ስመለስ ድካም እንደሚሰማኝ አሌ አይባልም። ሆኖም ደስተኛ ነኝ። እንዲሁም ይሖዋ ማንም የማይነጥቀኝን ደስታ ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ።” በመሆኑም መልካም ሥራ መሥራታችሁን በመቀጠል እናንተም ታላቅ ደስታ ታገኛላችሁ።