የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 10/01 ገጽ 7-8
  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • “የአምላክን ቤት” በአድናቆት መመልከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የምታከናውኑት መልካም ሥራ አይረሳም
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2019
  • ይምጡና ይጎብኙ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
km 10/01 ገጽ 7-8

ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?

1 በ778 ከዘአበ አንድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ክንውን ተፈጸመ። ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ” በራእይ ተመለከተ። ከዚያም ሱራፌሎች “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” እያሉ ይሖዋን ሲያወድሱት ሰማ። እንዴት ያለ አስደናቂ ክስተት ነው! በዚያን ወቅት ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት የሚፈታተን ጥያቄ አቀረበ። ስለሥራው ዓይነትም ሆነ ለሥራው ራሱን የሚያቀርበው ሰው ስለሚያገኘው ጥቅም ምንም የተባለ ነገር የለም። ቢሆንም ኢሳይያስ ሳያመነታ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ሲል መለሰ።​—⁠ኢሳ. 6:​1, 3, 8

2 የይሖዋ ሕዝቦች እሱ ያዘዛቸውን ሁሉ ለማድረግ ያላቸው ይህ ዓይነቱ የፈቃደኝነት መንፈስ ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። (መዝ. 110:​3 NW ) በአሁኑ ጊዜም ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረብ ለሚችሉ ሁሉ ልዩ ግብዣ በመቅረብ ላይ ይገኛል። አንተም እንደ ኢሳይያስ በፈቃደኝነት መንፈስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነህ?

3 የዘወትር እና ልዩ አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉ ተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች በየጊዜው ያስፈልጋሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደም ከፍተኛ ጉጉት ሊኖራቸውና ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይገባል። (ማቴ. 6:​33) ይህን ዓይነቱ አገልግሎት ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የማገልገል አጋጣሚ እንደሚከፍት እሙን ነው። እንዴት?

4 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚያስገኛቸው በረከቶች፦ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ይህን የአገልግሎት መብታቸውን እንዴት ያዩታል? አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ይላል:- “‘አዲሱ ዓለም መግባትና በዚያ ለማገኛቸው የጥንት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ዕድሜዬን ቁሳዊ ሀብት በማካበት ሳይሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዳሳለፍኩት መናገር መቻል እንዴት የሚያስደስት ይሆናል’ እያልኩ አስብ እንደነበር አስታውሳለሁ።”

5 ለ59 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈለ አንድ ወንድም “እያከናወንኩት ባለው ሥራ ቅር የተሰኘሁበት አንድም ቀን አልነበረም። ለምን? ምክንያቱም ራሳችንን በሙሉ ነፍስ ለይሖዋ ስናቀርብ ‘ልናደርገው የሚገባንን እንዳደረግን’ ስለምናውቅ እርካታ እናገኛለን” ብሏል።​—⁠ሉቃስ 17:​10

6 ለ62 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈለ ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ዕድሜ ልኬን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በማሳለፌ አንድም ቀን ተቆጭቼ አላውቅም። በስብከቱ ሥራ መካፈልና ለይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ታላቅ እድገት አስተዋጽዎ ማድረግ ምንኛ አስደሳች ነው!”

7 ወጣቶች፣ ከአሁኑ ራሳችሁን ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት አዘጋጁ፦ ወጣቶች ራሳቸውን ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማዘጋጀት ምን ማድረግ ይችላሉ? ኢየሱስ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ [ኪ]ሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” ብሏል። (ሉቃስ 14:​28) ለማንኛውም የግንባታ ውጥን ስኬታማነት ቅድመ ዝግጅትና እቅድ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ ወጣቶችም ወደፊት በይሖዋ አገልግሎት ለሚያሳልፉት ሕይወት የሚያደርጉትን ዝግጅት በጥንቃቄ ማጤናቸው ምንኛ የተገባ ነው! መንፈሳዊ ግቦቻቸው ላይ መድረስ ይችሉ ዘንድ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ጽኑ መሠረት ሊጣልላቸው ይገባል። ወጣት ከሆንክ ምን ያህል ጽኑ መሠረት እየጣልክ ነው? የሚከተለውን በጥንቃቄ ብትመረምር ትጠቀማለህ።

8 ይህን ልዩ የአገልግሎት መብት ‘ተቀበል’፦ በማቴዎስ 19:​12 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ነጠላነትን “ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” ሲል አበረታቷቸዋል። ለምን? ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ‘ስለ መንግሥተ ሰማያት’ ሲሉ ነው። በተመሳሳይም ጳውሎስ ‘ሳይባክኑ በጌታ መጽናት’ እንደሚያስችል በመግለጽ ነጠላነትን አበረታቷል። (1 ቆ⁠ሮ. 7:​32-35) ሆኖም አንዳንዶች ገና በልጅነታቸው በትዳር በመጠመዳቸው በነጠላነት አቅኚ ሆነው የማገልገል መብት አምልጧቸዋል። ወጣት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የቤተሰብ ኃላፊነት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ትኩስ ኃይላቸውን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል እንዲጠቀሙበት እናበረታታቸዋለን። ከጊዜ በኋላ ማግባት ቢወስኑ እንኳ በሕይወት እና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ያገኟቸው ተሞክሮዎች የተሻሉ ባል ወይም ሚስት እንዲሆኑ ያስችሏቸዋል። አንዳንዶች ለዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ያገቡ ሲሆን ከዚያ በኋላም አንድ ላይ ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ችለዋል።

9 ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ልባችሁ አይከፈል፦ እያንዳንዱ ወጣት ራሱን እንዲህ ብሎ ቢጠይቅ መልካም ነው:- ‘የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ግቤ የሙሉ ጊዜ ሰብዓዊ ሥራ መያዝ ነው ወይስ ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ማገልገል?’ እርግጥ ነው ሁለተኛውን አማራጭ መከተል መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቃል። ሰብዓዊ ሥራም ቢሆን እንዲሁ መሥዋዕትነት ማስከፈሉ አይቀርም! በመጨረሻ ዘላቂና ጠቃሚ የሆነ ውጤት ያለው የትኛው ነው? ኢየሱስ ምንም የማያሻማ መልስ ሰጥቷል። በማቴዎስ 6:​19-21 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው እንዲህ ብሏል:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።” ልባችን በሙሉ ነፍስ ይሖዋን በማገልገል ፋንታ ዓለማዊ ሥራን ወይም ቁሳዊ ነገሮችን እንድናሳድድ አያታልለን። ልንከተለው የሚገባ ብቸኛ ጠቃሚ ግብ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረት የሱን ልብ ደስ ማሰኘት መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን። (ምሳሌ 27:​11) ወጣት እያለን በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን በአንደኛ ደረጃ ማስቀመጣችን መዝገባችን የት እንዳለና መንግሥቱን ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ያሳያል። ‘የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ እንደምታደርግና ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር እንደማይጨምር’ አስታውሱ። (ምሳሌ 10:​22) ወጣቶች ይሖዋ ለሚያደርግላቸው ሁሉ እነርሱም በምላሹ መልካም ነገር በማድረግ ልባቸው በምን ላይ እንዳተኮረ የሚያሳዩበት ግሩም አጋጣሚ አላቸው።

10 አቅኚዎች በሥነ ምግባር ንጹሖች መሆን አለባቸው፦ መዝሙራዊው “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ መልስ ሲሰጥ “ቃልህን በመጠበቅ ነው” ብሏል። (መዝ. 119:​9) የይሖዋን ቃል መጠበቅ በሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ካለው ከማንኛውም ብልሹ ሥነ ምግባር መራቅን ይጨምራል። ሰይጣን ወጣቶች መንፈሳዊ ግባቸው ላይ እንዳይደርሱ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች መካከል በኢንተርኔት የሚታዩ ወሲባዊ ስዕሎች፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ፣ ወራዳ የሆነ ሙዚቃና መዝናኛ እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ይገኙበታል። በእነዚህ የሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ ቆራጥነት ያስፈልጋል። በእነዚህ ነገሮች የተጠላለፍክ ወጣት ከሆንክ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከማመልከትህ በፊት ሽማግሌዎችን በማነጋገር እነዚህን ጉዳዮች አስተካክል። ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል ንጹህ ሕሊና መያዝ ወሳኝ ነው።​—⁠1 ጢ⁠ሞ. 1:​5

11 ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖርን ተማር፦ በአቅኚነት አገልግሎት ስኬታማ ለመሆን አንዱ አስፈላጊ ነገር ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር መቻል ነው። ራስህን እንዲህ ብለህ ብትጠይቅ ጥሩ ነው:- ‘ሌሎች ሐሳቤን የማይጋሩ ከሆነ በቶሎ ቅር እሰኛለሁ? ሌሎች ከእኔ ጋር በቀላሉ መግባባት ይችላሉ?’ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ማድረግ ካስፈለገህ ከአሁኑ እርምጃ ውሰድ። እንዲህ ማድረግህ ከሌሎች ጋር በቀላሉ ተግባብቶ መኖርና መሥራት እንድትችል ይረዳሃል።

12 ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በማዳበር መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ ማንበብን የሚጨምር ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም አውጣ። ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ ንቁ ተሳትፎ አድርግ። እነዚህን ነገሮች በተግባር በማዋል ማደግህ እንዲገለጥ ማድረግ ትችላለህ። (1 ጢ⁠ሞ. 4:​15) ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ ከአሁኑ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ይጠብቃቸዋል!

13 ወላጆች ልጆቻችሁን አሰልጥኑ፦ ወላጆች ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ አድርገው እንዲከታተሉ ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ? ኢየሱስ “ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል” ብሏል። (ሉቃስ 6:​40) በሚገባ የሰለጠነ ተማሪ የትጉህ መምህሩን መልካም ባህርያት ሁሉ እንደሚያንጸባርቅ የታወቀ ነው። ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ‘ለአምላክ ያደሩ’ እንዲሆኑ ሲያሰለጥኗቸው ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሯቸው መያዝ አለባቸው። (1 ጢ⁠ሞ. 4:​7 NW ) ልጆች ወላጆቻቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን አመለካከት የማንጸባረቅ ዝንባሌ ስላላቸው ወላጆች ራሳቸውን እንዲህ ብለው ቢጠይቁ ተገቢ ነው:- ‘የይሖዋን እውነተኛ አምልኮ ለማስፋፋት በቤቴልም ሆነ በመስኩ ለሚከናወነው ሥራ አድናቆት አለኝ? የይሖዋ አገልግሎት ልጆቻችን ሊመርጧቸው ከሚችሏቸው ሥራዎች ሁሉ የላቀው እንደሆነ አድርጌ አምንበታለሁ?’ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎትና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ለሚያከናውኑት ሥራ ያለን ልባዊ አድናቆት በልጆቻችንም ውስጥ ተመሳሳይ ስሜት ለማሳደር ያስችለናል።

14 ሕልቃና እና ሐና ለእውነተኛው አምልኮ ጥልቅ አድናቆት ነበራቸው። በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያን ወላጆች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። በጥንት እስራኤል በማደሪያው ድንኳን “በጌታ በእግዚአብሔር ፊት” በዓመት ሦስት ጊዜ መቅረብ ይጠበቅባቸው የነበረው እስራኤላውያን የሆኑ ወንዶች ብቻ ነበሩ። ቢሆንም ሕልቃና “በየዓመቱ” ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ በዚህ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል መሥዋዕት ለማቅረብ በእግር ሳይሆን አይቀርም ወደ 30 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት ይጓዝ ነበር። (ዘጸ. 23:​17፤ 1 ሳ⁠ሙ. 1:​3, 4, 9, 19፤ 2:​19) ይህ የቤተሰብ ራስ መላው ቤተሰብ እሱ ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረው አመለካከት እንዲኖረው ይፈልግ እንደነበር ግልጽ ነው።

15 ሐናም ለእውነተኛው አምልኮ የባሏ ዓይነት አመለካከት ነበራት። በማደሪያው ድንኳን ለሚከናወነው እውነተኛ አምልኮ የበኩሏን ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባት ይሰማት ነበር። ሐና፣ ይሖዋ ልጅ ከሰጣት በማደሪያው ድንኳን እንዲያገለግል ለመስጠት ተስላ ነበር። (1 ሳ⁠ሙ. 1:​11) በሙሴ ሕግ አንድ ባል ሚስቱ ተገቢ ያልሆነ ስእለት ብትሳል፣ ስእለቷን ውድቅ የማድረግ መብት ነበረው። (ዘኁ. 30:​6-8) ይሁን እንጂ ሕልቃናም ይህን የእውነተኛ አምልኮ መግለጫ በመደገፍ በሐና ስእለት ተስማምቷል።​—⁠1 ሳ⁠ሙ. 1:​22, 23

16 እነዚህ ወላጆች ያሳዩት አድናቆትና ግሩም ዝንባሌ በልጃቸው በሳሙኤል ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበርን? እንዴታ! ገና ብላቴና የነበረው ሳሙኤል በፈቃደኝነት እና በታማኝነት የተሰጠውን ሥራ ያከናውን የነበረ ሲሆን በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ለተጨማሪ ውድ መብቶች ስልጠና አግኝቷል። ሕልቃና እና ሐና ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ለሚያከናውነው አገልግሎት ይሰጡ የነበረው ትኩረት የሥራ ኃላፊነቶቹን ከተቀበለ በኋላም ቢሆን አልተቋረጠም ነበር። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈል ማበረታቻና ድጋፍ ለመስጠት ዘወትር ይጎበኙት ነበር።​—⁠1 ሳ⁠ሙ. 2:​18, 19

17 ሕልቃና እና ሐና በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያን ወላጆች እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው! ልጆቻችን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መብትን ከልባችን ስናደንቅ ሲሰሙና የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደም የምናሳየውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ሲመለከቱ የእነሱም ልብ ሌሎችን የማገልገል ዝንባሌ ያድርበታል። ብዙ ወላጆች ይህን ጤናማ ዝንባሌ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ በማሳደር ረገድ ተሳክቶላቸዋል። አንዲት የሰባት ዓመት ልጅ እንዲህ ብላ ጽፋለች:- “ሳድግ ቤቴል ገብቼ ልሠራቸው የምፈልጋቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። እነዚህም (1) የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔቶችን ታይፕ ማድረግ (2) በሥዕል ክፍሉ ውስጥ መሥራትና (3) የታጠቡ ልብሶችን ማጣጠፍ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ማንኛውንም ሥራ ቢሰጠኝም ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ።” በልጆቻችን ልብ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ሲዳብር መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነው!

18 ወጣቶች ‘ዓለሙም ምኞቱም እንደሚያልፍና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም እንደሚኖር’ አስታውሱ። (1 ዮሐ. 2:17) የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጨምሮ መንፈሳዊ ግቦችን መከታተላችሁን ቀጥሉ። ወላጆችም ልጆቻቸው ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ ያበረታቱ የነበሩትን የጥንት ታማኞች ምሳሌ ኮርጁ። (2 ጴ⁠ጥ. 3:11, 12) ይህ ‘ለአሁንና ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው’ ወጣት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሚቻላቸው አቅም ሁሉ ታላቁን ፈጣሪ እንዲያገለግሉ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ።​—⁠1 ጢ⁠ሞ. 4:​8፤ መክ. 12:​1

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ