“የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተማርከውን እየሠራህበት ነውን?
1 በዚህ ዓመት በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘ ማንኛውም ሰው የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን የገቡትን ቃል ለመፈጸም ታጥቀው መነሳታቸውን መመልከት ይችላል። (ማቴ. 28:19, 20) ወደ ቤትህ ስትመለስ የትኞቹን መመሪያዎች በግል ሕይወትህም ሆነ በመስክ አገልግሎት ልትሠራባቸው ቆርጠህ ነበር?
2 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ለትምህርት ይጠቅማሉ:- የመጀመሪያው ዕለት ጭብጥ 2 ጢሞቴዎስ 3:16ን የሚያጎላ ነበር። የጭብጡ ቁልፍ ንግግር “የአምላክን ቃል ለማስተማር በሚገባ የታጠቁ” ለመሆን የአምላክን ቃል ከፍ አድርገን ልንመለከተው፣ ከሰብዓዊ አመለካከት ወይም ወግ የላቀ አክብሮት ልንሰጠውና አዘውትረን ልንጠቀምበት እንደሚያስፈልግ ገልጿል። በአገልግሎታችን እንዲረዳን በየዕለቱ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይና ከሁሉ የላቀውን የእርሱን ፍሬ ማለትም ፍቅርን ለማዳበር ጥረት ማድረግ አለብን። የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት እንደ አገልጋዮች አድርጎ እንዲያሠለጥነን ፈቃደኞች መሆን አለብን።
3 “ሌሎችን እያስተማርን ራሳችንንም ማስተማር” በሚል ርዕስ ዓርብ ዕለት የቀረበው ሲምፖዚየም (1) በሁሉም የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ዘርፎች የአምላክን ሕግጋት አጥብቆ በመከተል፣ (2) በትጋት የማጥናት ልማድ በማዳበር፣ (3) ዲያብሎስ መጠቀሚያ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን የልብና የአእምሮ ዝንባሌዎች እንዲሁም ሁኔታዎች በማስወገድ ረገድ አርአያ መሆን እንዳለብን አብራርቷል። ከዚያም በዓለም ላይ እንደወረርሽኝ ከተስፋፉት ወሲባዊ ስዕሎች ቤተሰባችንን የምንጠብቅባቸውን ተግባራዊ የሆኑ መንገዶች ተምረናል። ወላጆች ለቅጽበትም ቢሆን የጾታ ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ነገር ባለመመልከት ምሳሌ እንዲሆኑና የልጆቻቸውን የኢንተርኔትና የቴሌቪዥን አጠቃቀም እንዲቆጣጠሩ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። በአርቡ ፕሮግራም ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ የትኞቹን በተግባር ማዋል ጀምረሃል?
4 የዕለቱ የመደምደሚያ ንግግር ከይሖዋ የሚገኘውን ብርሃን ከፍ አድርገን ለማየት፣ ለአምላክ ታማኝ ከሆነው የቅቡዓን ክፍል ጎን ለመቆምና ለይሖዋ ሕዝቦች ሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮታል። አዲስ የወጣውን የኢሳይያስ ትንቢት—ለሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2 እንደደረሰህ እንድታነበው እናበረታታሃለን።
5 ሌሎችን ለማስተማር ብቁ ሆኖ መገኘት:- የሁለተኛው ቀን የጭብጡ ጥቅስ 2 ጢሞቴዎስ 2:2 ነበር። የቅዳሜ ጠዋቱን ሲምፖዚየም ስታዳምጥ (1) የሚገባቸውን መፈለግ፣ (2) ፍላጎታቸውን መኮትኮትና (3) ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማር እንዴት እንደሚቻል የቀረቡትን ሐሳቦች አስተውለሃል? ከቤት ወደ ቤት ለምታነጋግራቸው ሰዎች ቢያንስ አንድ ጥቅስ ስለ ማንበብና ለሚቀጥለው ጉብኝት መሠረት ስለ መጣል የተማርከውን በተግባር እያዋልክ ነው?
6 የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስን የመኮረጅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። እሱን በይበልጥ ለመምሰል እየተጣጣርክ ያለኸው በየትኞቹ ዘርፎች ነው? ቀጥሎ “ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ ናችሁ?” በሚል ርዕስ በቀረበው ንግግር በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን ለመሸከምም ሆነ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የምንጣጣርባቸውን መንገዶች ተመልክተን ነበር። እንዲሁም በዕለቱ በቀረበው ሁለተኛ ሲምፖዚየም ላይ በተማርከው መሠረት ‘ከቲኦክራሲያዊው ትምህርት ሙሉ በሙሉ’ እንዴት መጠቀም የምትችል ይመስልሃል? በግል ጥናትም ሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ ትኩረታችን ሳይከፋፈል መቆየት የሚያስችሉንን የትኞቹን ሐሳቦችስ ተግባራዊ አድርገሃል?
7 በቅርቡ የሚወጣው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቀሙ የተባለ መጽሐፍ በንግግርና የአምላክን ቃል በማስተማር ችሎታችን ረገድ እድገት እንድናደርግ እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁባቸው የንግግር ችሎታዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥባቸዋል። በአዲሱ የመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ እያንዳንዱ ትምህርት ምን ማድረግ እንዳለብን፣ ይህን ማድረጉ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና እንዴትስ ልናደርገው እንደምንችል አጠር ባለ መንገድ የሚያሳይ ሳጥን አለው። ተግባራዊ መልመጃዎችም ይዟል። እህቶች ክፍላቸውን ሲያቀርቡ መርጠው የሚጠቀሙባቸው 29 መቼቶች አሉ። በትምህርት ቤቱ አደረጃጀት ላይ የተደረጉት እነዚህ ለውጦች ወደፊት በሥራ ላይ ይውላሉ። ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እንድትችል በየሳምንቱ ጥሩ የጥናትና የዝግጅት ልማድ አለህ?
8 ከጊዜው የተነሣ አስተማሪዎች ሁኑ:- ዕብራውያን 5:12 እሁድ ዕለት ለተደረገው ስብሰባ የአድማጮችን አእምሮ አዘጋጅቶ ነበር። “የሚልክያስ ትንቢት ለይሖዋ ቀን ያዘጋጀናል” በሚል ርዕስ ጠዋት የቀረበው ሲምፖዚየም ከታላቁና አስፈሪ ከሆነው የይሖዋ ቀን በሕይወት ለመትረፍ ለአምላክ ምርጣችንን እንድንሰጥና ማንኛውንም ዓይነት ክህደት እንድንጠላ አጥብቆ አሳስቦናል። “የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ” የሚለው ድራማ ቆሬና ተባባሪዎቹ የነበራቸው ኩራት፣ የሥልጣን ጥማት፣ ቅናትና ያለቦታው የገባ ታማኝነት በይሖዋ ላይ ሳይቀር ወደ ማመፅ እንዴት እንደመራቸው ጥሩ በሆነ መንገድ አሳይቷል። ከድራማው ቀጥሎ የቀረበው ንግግር ዛሬ በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ለአምላካዊ ሥልጣን መገዛት ባለው አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነበር። “ለአሕዛብ ሁሉ እውነትን እያስተማሩ ያሉት እነማን ናቸው?” የሚል ርዕስ ያለው የሕዝብ ንግግር እንዲያው በአፏ ብቻ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አስተምራለሁ ከምትለው ሕዝበ ክርስትና በተቃራኒ በተግባር ይህን እያደረጉ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
9 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የተሻልን የቃሉ አስተማሪዎች እንድንሆን እያሰለጠነን ነው። ‘ራሳችንንም የሚሰሙንንም ለማዳን እንድንችል ለራሳችንና ለትምህርታችን እየተጠነቀቅን’ የተማርነውን በተግባር ላይ እናውል።—1 ጢሞ. 4:16