እስከ ምድር ዳር ድረስ—መመስከር
እስከ ምድር ዳር ድረስ የተባለውን ቪዲዮ ደጋግመው የሚመለከቱት እነማን ናቸው? ሚስዮናዊ የመሆን ግብ ያላቸው ናቸው። ለምን? ምክንያቱም ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ጋር ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ስለሚረዳቸው ነው። ቪዲዮው ምስክርነት የመስጠቱን ሥራ ወደ ‘ምድር ዳርቻዎች ሁሉ’ ለማስፋፋት የተቋቋመውን የዚህን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት የሚያሳይ ነበር። (መዝ. 22:27) ይህን ቪዲዮ መመልከትህ በጣም አስፈላጊ ለሆነው ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ያለህን አድናቆት ከመጨመሩም በላይ እንቅስቃሴህን እንድታሳድግ ያነሳሳሃል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች ተመልከት:- (1) በ1940ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የይሖዋ ድርጅት ዋና ትኩረቱን ያደረገው በምን ላይ ነበር? (ሥራ 1:8) (2) በ1942 ምን አስገራሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን በማግኘት ላይ ነበር? ትኩረታችን ከጠቅላላው ዓለም ትኩረት የተለየ የነበረው እንዴት ነው? (ራእይ 17:8፤ w89 4/15 ገጽ 14 አንቀጽ 12) (3) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን የሰላም ወቅት ለመጠቀም ምን ዝግጅት ተደረገ? (አዋጅ ነጋሪዎች ገጽ 522 አንቀጽ 1-2) (4) የጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍል ተማሪዎች ከነበራቸው ባሕርያት ውስጥ የቱን ታደንቃለህ? (5) ጊልያድ ባሳለፋቸው የመጀመሪያዎቹ 50 ዓመታት ምን ያህል ተማሪዎች አስመርቋል? ተማሪዎቹ የተላኩት ወደ ስንት አገሮች ነው? (6) ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ምን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይቀስማሉ? (7) ብቃት ያለው ሚስዮናዊና የአምላክ ቃል አስተማሪ ለመሆን የሚያስችለው ምንድን ነው? (8) የሚስዮናዊ ሕይወት ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ችግሮችን መቋቋምስ ይጠይቃል? (9) ሚስዮናውያን ስለ አኗኗራቸው ምን ይሰማቸዋል? የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረጋቸው ምን ልዩ ደስታ ሊያገኙ ችለዋል? (10) በሺዎች የሚቆጠሩት ሚስዮናውያን እስከ ዛሬ ድረስ ምን አከናውነዋል? ምሳሌዎች ጥቀስ። (11) ምሥራቹን ለመስበክ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለሄዱት ወንድሞችና እህቶች ምን ይሰማሃል? (12) ሚስዮናውያኑ የተዉት አርአያ ምን እንድታደርግ ያበረታታሃል? ለምን?