መንግሥቱን ማስቀደማችሁን ቀጥሉ
1 የኢኮኖሚ ተጽእኖዎች ወይም ሌሎች ችግሮች እያሉብንም በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ማስቀደምና በዚያው መቀጠል ቀላል አይደለም። አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም መንግሥቱን ማስቀደማችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ከስብሰባዎች እንድንቀር የሚያደርገን ወይም ወደ አገልግሎት እንዳንወጣ እንቅፋት የሚሆንብን የሥራ ግብዣ ቢቀርብልንስ? በዚህ ጊዜ መንግሥቱን በሕይወታችን ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ልንሰጠው ይገባል?
2 ጠንካራ እምነት ያስፈልጋል:- እምነታችን እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች በሚፈተንበት ጊዜ መንግሥቱን ማስቀደማችንን ከቀጠልን መለኮታዊ ድጋፍ እንደምናገኝ ይሖዋ የገባውን ቃልና ኢየሱስ የሰጠውን ዋስትና መዘንጋት የለብንም። (መዝ. 37:25፤ ማቴ. 6:31-34) ዓለማዊ ተጽዕኖዎችና ግፊቶች ዕይታችንን ሊያደበዝዙብንና መንግሥቱን ማስቀደማችንን እንዳንቀጥል ሊያግዱን ይችላሉ። አንዳንዶች በሥራ ቦታ ጎልቶ መታየት ወይም ገንዘብ ነክ ጥቅሞችን ማግኘት በሕይወታቸው ውስጥ ዓቢይ ቦታ እንዲይዝ ፈቅደዋል። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ጳውሎስ እኛም በሕይወት ውስጥ የላቀ ዋጋ ያለው ምን እንደሆነ በጥንቃቄ ማመዛዘን ያስፈልገናል።—ፊልጵ. 3:7, 8
3 ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልግ ይሆን? አንዲት አስፋፊ እንዲህ ብላለች:- “ቀልቤ ሙሉ በሙሉ ያረፈው በሥራዬ ላይ ሲሆን ሥራዬን ከምንም ነገር አስበልጬ እወድ ነበር። አብዛኛውን ጊዜዬን ለሥራ ጉዳይ እያዋልኩም ቢሆን ምሥክር ሆኜ መቀጠል እንደምችል ይሰማኝ ነበር።” ነገር ግን ይሖዋን ለማገልገል የበለጠ ማድረግ እንደምትችል ሕሊናዋ ነጋ ጠባ ይወተውታት ነበር። ከጊዜ በኋላ ለመንፈሳዊ እድገቷ ደንቃራ የሆነባትን ሥራዋን እርግፍ አድርጋ ተወችው። ራስዋን ሙሉ በሙሉ በመንግሥቱ ሥራ ካስጠመደች በኋላ እንዲህ ለማለት ችላለች:- “አሁን ሕይወቴ በይሖዋ ፊት ስኬታማ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ደግሞም ከሁሉ የሚበልጠው ይሄ ነው።”
4 ደስ የሚለው ብዙዎች ሰብዓዊ ሥራዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙላቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን በመተውና ሕይወታቸውን ቀላል በማድረግ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገብተዋል። በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ነጠላ የሆኑ ወጣት የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች እንዲህ በማድረጋቸው አስደሳች የአገልግሎት መብቶችን በማግኘት ተባርከዋል። ጳውሎስ የተወውን ግሩም ምሳሌ በመከተል መሠረታዊ በሆኑት ቁሳዊ ፍላጎቶች ይረካሉ።—1 ቆሮ. 11:1፤ 1 ጢሞ. 6:6-8፤ ዕብ. 13:5
5 ስለ ሕይወት ባለን አመለካከት ዓለም ሊያፌዝ ቢችልም የይሖዋን በረከት እናገኛለን። (1 ቆሮ. 1:26-31) ይሖዋ በእኛ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠቀምብንና የሰጠንን ሥራ መፈጸም እንችል ዘንድ እንደሚረዳን ማወቁ የሚያበረታታ አይደለም? ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ለማወጅ ያለን የአሁኑ አጋጣሚ በፍጹም አይደገምም። ስለዚህ በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን ማስቀደማችንን የምንቀጥልበት ጊዜ አሁን ነው።