አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ለማስተዋወቅ የሚረዱ አቀራረቦች
“ብዙ ሰዎች በአምላክ ያምናሉ ቢባል እንደሚስማሙ አያጠራጥርም። በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር እንዳለ ይስማማሉ። ይሁን እንጂ ሊስማሙ ያልቻሉት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ነው።” ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ካበረከትክ በኋላ ትምህርት 1ን ገልጠህ አወያየው።
“በዛሬው ጊዜ የቤተሰብ ሕይወት በችግሮች የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ የቤተሰብ ደስታ ለማግኘት የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው? ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?” የሚሰጠውን መልስ ካዳመጥክ በኋላ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ የሚያስገኘውን እውነተኛ ቁልፍ ግልጽ አድርጎ እንዳስቀመጠ አብራራ። ኢሳይያስ 48:17ን አንብብ። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከተባለው ብሮሹር ትምህርት 8ን አውጣና እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል የሚመለከት አስተማማኝ መመሪያ የሚሆኑ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አሳየው። በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብና ሰውየው መልሶቻቸውን ለማንበብ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቅ።
“ይህ ብሮሹር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ጠቅለል ባለ ሁኔታ አጥንቶ መሸፈን ያስችላል። በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ለዘመናት ሰዎችን ሲያስጨንቁ ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?” ትምህርት 5ን ግለጥና በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብ። የቤቱን ባለቤት ትኩረቱን የሳበው ጥያቄ የቱ እንደሆነ ጠይቀውና ለጥያቄው መልስ የሚሰጠውን አንቀጽ(ጾች) አንብብ። ተስማሚ የሆኑ ጥቅሶችን አውጥታችሁ ተመልከቱ። እንደዚህኛው ጥያቄ ሁሉ ለሌሎቹም ጥያቄዎች በቀላሉ አጥጋቢ መልስ ማግኘት እንደሚቻል ግለጽለት። በሌላ ጥያቄ ላይ ለመወያየት በድጋሚ ተመልሰህ ለመምጣት ሐሳብ አቅርብ።
“በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚታዩት የዓመፅ ድርጊቶች መንስኤው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ ካለማሰልጠናቸው የመነጨ ነው? ወይስ ከበስተጀርባው የዲያብሎስ ተጽዕኖ አለ ይላሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ሰውየው የዲያብሎስ ተጽዕኖ አለ ብሎ ከመለሰ ራእይ 12:9, 12ን አንብብለት። ዲያብሎስ በዓለማችን ላይ ሁከትና ብጥብጥ በማስፋፋት ረገድ ያለውን ሚና ጥቀስ። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ትምህርት 4ን ግለጥና ግለሰቡ ዲያብሎስ ከየት መጣ የሚል ጥያቄ አንስቶ ያውቅ እንደሆነ ጠይቀው። ቀጥለህ የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች አንብብና ተወያዩበት። ሰውየው በትምህርት ቤቶች ለሚታየው ዓመፅ መንስኤው “ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ አለማሰልጠናቸው ነው” ካለ ደግሞ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አንብብና ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ ያበረከቱትን መጥፎ ባሕርያት ጥቀስ። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ትምህርት 8ን አውጣና አንቀጽ 5ን አንብበህ ውይይቱን ቀጥል።
“የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ለመመሥረት የሚያስፈልገንን እውቀት ፈጣሪ ይሰጠናል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልዎታል?” የሚሰጠውን መልስ ካዳመጥክ በኋላ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር አስተዋውቀው። ትምህርት 8ን ግለጥና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ምን እንደሚጠበቅበት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደያዘ አብራራ። ከብሮሹሩ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ብሮሹሩን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ልታሳየው እንደምትችል ግለጽለት።
“በአሁኑ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመወጣት ጸሎት በእርግጥ ሊረዳን ይችላል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙዎች ጸሎት ውስጣዊ ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። [ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።] ሆኖም አንድ ሰው ለጸሎቱ ምንም መልስ እንዳላገኘ ሊሰማው ይችላል። [አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 7 ላይ ግለጥ።] ይህ ብሮሹር ጸሎት ምን ያህል ሊጠቅመን እንደሚችል ያብራራል።”
“በዓለም ዙሪያ ሃይማኖቶች የበዙት ለምን እንደሆነ ከጎረቤቶቻችን ጋር እየተነጋገርን ነበር። አብዛኞቹ የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሆኖ ሳለ ይህን ያህል ሃይማኖታዊ ዝብርቅ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 13ን ግለጥና በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች አንብብ።] ይህን ትምህርት በማንበብ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሊያገኙ ይችላሉ።”
ለአንድ ሰው መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት ካበረከትክ በኋላ አንድ አጭር አንቀጽ ልታነብለት ትችል እንደሆነ ጠይቀው። ፈቃደኛ ከሆነ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ብሮሹር ትምህርት 5ን አውጣ። በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች አሳየውና አንቀጽ አንድን ስታነብለት ለመጀመሪያው ጥያቄ የተሰጠውን መልስ እንዲያዳምጥ ጋብዘው። አንቀጹን ካነበብክ በኋላ ጥያቄውን ጠይቀውና የሚሰጥህን መልስ አዳምጥ። ከዚያም ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘውና እሺ ብሎ ከወሰደ ቀጥሎ ለቀረቡት ሁለት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ለመስማት በሌላ ጊዜ ተመልሰህ ለመምጣት ቀጠሮ ያዝ።