እውቀት መጽሐፍን ለማበርከት የሚረዱ አቀራረቦች
መጽሐፍ ቅዱስን በእጅህ ይዘህ እንዲህ በማለት ውይይት ክፈት:- “ዛሬ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እያነበብንላቸው ነበር። እንዲህ ይላል . . .” ዮሐንስ 17:3ን አንብብና ይህን ጥያቄ አቅርብ። “ትክክለኛው እውቀት ምን ሊያስገኝ እንደሚችል አስተዋሉ?” [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አንድ ሰው ይህን ዓይነት እውቀት ማግኘት የሚችለው ከየት ነው? የሚሰጥህን መልስ ካዳመጥክ በኋላ እውቀት መጽሐፍን አሳየውና እንዲህ በል:- “ይህ መጽሐፍ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ላሏቸው የጋራ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ያስጨብጣል።” የአርዕስት ማውጫውን አሳየውና ሰውየው ስለ እነዚህ ጥያቄዎች አስቦ ያውቅ እንደሆነ ጠይቀው።
“በእኛ በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ሲደርስ የምንመለከተው ግፍና ስቃይ በእርግጥ አምላክን ያሳስበዋል ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደሚወድደንና በችግር ጊዜም እንደሚረዳን ማረጋገጫ ይሰጠናል።” ከመዝሙር 72:12-17 ላይ የተወሰኑ ቁጥሮችን አንብብ። እውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ 8ን አውጣና ምዕራፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሚጠይቁት ‘አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ የሚያጽናና መልስ እንደሚሰጥ አሳየው። የሚቻል ከሆነ እዚያው አሊያም ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ ስትመጣ ከአንቀጽ 3 እስከ 5 ላይ የቀረቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ተወያዩበት።
“አብዛኞቻችን የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት አጥተናል። እነዚህን ሰዎች በድጋሚ እናገኛቸው ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት ሊነሱ እንደሚችሉ ኢየሱስ በተግባር አሳይቷል። [ዮሐንስ 11:11, 25, 44ን አንብብ።] ምንም እንኳ ይህ የተከናወነው ከብዙ ዘመናት በፊት ቢሆንም አምላክ ወደፊት ሊያደርግልን ቃል የገባልንን ነገር የሚያሳይ ነው።” እውቀት መጽሐፍ ገጽ 85 ገልጠህ ለስዕሉ የተሰጠውን መግለጫ አንብብ። ከዚያም በገጽ 86 ላይ የሚገኘውን ስዕል አሳየውና በስዕሉ ላይ ሐሳብ ስጥ። “ሰዎች የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምን እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጋለህ?” ብለህ በመጠየቅ ለሚቀጥለው ጉብኝት መሠረት ጣል። ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ምዕራፍ 6ን አወያየው።
“የሰው ልጆች ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚጓጉት ለምንድን ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?” የሚሰጠውን መልስ ካዳመጥክ በኋላ እውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ 6ን አውጣና አንቀጽ 3ን አንብብ። በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች አብራራ። በአንቀጹ መጨረሻ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብና ሰውየው መልሶቹን ማወቅ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀው። አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠህ በቀጣዮቹ ጥቂት አንቀጾች ላይ ተወያዩ።
“ሰዎች በሚከተለው አባባል ያምኑ እንደሆነ እየጠየቅናቸው ነበር።” ዘፍጥረት 1:1ን አንብብና “እርስዎስ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ?” ብለህ ጠይቀው። የሚስማማ ከሆነ እንዲህ በል:- “እኔም እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር ከሆነ ለክፋትም ተጠያቂው እርሱ ነው ብለው ያስባሉ?” የሰውየውን መልስ ካዳመጥክ በኋላ መክብብ 7:29ን አንብብ። ከዚያም እውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ 8ን ግለጥና አንቀጽ 2ን አንብብ። በዘፍጥረት 1:1 ላይ ባለው ሐሳብ የማይስማማ ከሆነ ግን ፈጣሪ እንዳለ የሚያሳየውን ማስረጃ እንዲመረምር አበረታታው።—ማመራመር መጽሐፍ ገጽ 83-85 ተመልከት።
“በጊዜያችን የሥነ ምግባር ደረጃዎች በፍጥነት የሚለዋወጡ ከመሆናቸው የተነሳ ለሕይወታችን አስተማማኝ የሆነ መመሪያ ያስፈልገናል ቢባል አይስማሙም? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንም ለዘመናዊው ኑሮና አስደሳች ለሆነ የቤተሰብ ሕይወት ተግባራዊ ምክር ይሰጣል።” ከዚያም እውቀት መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 2ን ግለጥና አንቀጽ 10ን እና የአንቀጽ 11ን የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር እንዲሁም 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።
“ስለ እኛም ሆነ ስለ ምድር የወደፊት ዕጣ ማወቅ ይፈልጋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ ወደፊት ምድር ገነት ትሆናለች በማለት ይናገራል! አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ከፈጠረ በኋላ ያስቀመጣቸው በገነት ውስጥ ነበር። በዚያ ገነት ውስጥ ሕይወት ምን ሊመስል ይችል እንደነበር ይህንን አገላለጽ ልብ ይበሉት።” እውቀት መጽሐፍ ገጽ 8ን አውጣና “ሕይወት በገነት ውስጥ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር አንቀጽ 9ን አንብብ። ከዚያም በአንቀጽ 10 ላይ ያለውን ሐሳብ ካወያየኸው በኋላ አንቀጹ ውስጥ የተጠቀሰውን ኢሳይያስ 55:10, 11ን አንብብ። ወደፊት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት በሚናገሩት ከ11-16 ባሉት አንቀጾች ላይ ውይይታችሁን ለመቀጠል ግብዣ አቅርብለት።