ለጊዜያችን የሚሆኑ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ልብ እንድንል የቀረበ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ
ሁላችንም ለጊዜያችን የሚሆኑ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች በተባለው የቪዲዮ ፊልም ከቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ የተማርናቸውን ትምህርቶች ልብ በማለት ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጠኝነት ማጠናከር እንችላለን። ፊልሙን ከመመልከታችሁ በፊት ዘኍልቍ ምዕራፍ 25ንና ማግኘት የምትችሉ ከሆነ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል—ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 419 አንቀጽ 3-5 ላይ ያለውን ሐሳብ እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሩ:- ሞዓባውያን እነማን ነበሩ? ይሖዋ ሞዓባውያንን እንዳይወጋቸው ሙሴን ያዘዘው ለምን ነበር? (ዘዳ. 2:9) በለዓም የእስራኤልን ብሔር ለማጥፋት በተንኮል ሞዓባውያንን የተጠቀመው እንዴት ነው? በርካታ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ እያሉ የገጠማቸውን ወሳኝ ፈተና ሳያልፉ መቅረታቸውን ሁልጊዜ ማስታወስ የሚኖርብን ለምንድን ነው?—1 ቆሮ. 10:11, 12
ለጊዜያችን የሚሆኑ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ስትመለከቱ በዛሬው ጊዜ ታማኝነታችንን ለመጠበቅና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት እንችል ዘንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው የሚገቡንን የሚከተሉትን አራት የሕይወት ዘርፎች አስቡ። (1) አመለካከት:- አንዳንድ እስራኤላውያን ለይሖዋና ለዝግጅቶቹ የተሳሳተ አመለካከት ያሳዩት እንዴት ነው? እኛስ ከዚህ በተቃራኒ ምን ዓይነት ዝንባሌ ማሳየት ይኖርብናል? (2) ጓደኝነት:- እስራኤላውያን ከሞዓባውያን ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ይሖዋ ያልፈለገው ለምንድን ነው? (ዘጸ. 34:12፤ ምሳሌ 13:20) ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (3) ሥነ ምግባር:- መጥፎ ጓደኝነት 23, 000 የሚያህሉ እስራኤላውያን ምን ዓይነት ከባድ ኃጢአት እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል? (1 ቆሮ. 10:8) በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም ያደረሳቸው ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? (4) አምልኮ:- እስራኤላውያን የአምልኮታቸው ንጽሕና የተፈተነው እንዴት ነበር? በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች በየትኛው ስውር የጣዖት አምልኮ ሊሸነፉ ይችላሉ? ይሁን እንጂ ራሳችንን ከዚህ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?—ቆላ. 3:5
ያሚን የሥነ ምግባር ንጽሕናውን በመጠበቁ የተባረከው እንዴት ነው? የአስተዳደር አካል በዚህ የቪዲዮ ፊልም አማካኝነት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ማስተላለፍ የፈለገው ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ምንድን ነው? የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ቤተሰብህ ይህን የቪዲዮ ፊልም በተደጋጋሚ እንዲመለከት ማድረጉ ጥበብ ነው የምትለው ለምንድን ነው?