የኢትዮጵያ ዓመታዊ የመስክ አገልግሎት ሪፖርት፦
የተገኘው ጭማሪ፦ በይሖዋ እርዳታ በአስፋፊዎች ቁጥር 5 በመቶ ጭማሪ አግኝተናል። በአገልግሎት ዓመቱ ውስጥ አምስት አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት ተደርጓል። ትልቁ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር የተገኘው በነሐሴ ሲሆን 6, 685 ነበር። የዓመቱ አማካይ የአስፋፊዎች ቁጥር 6, 471 ነበር። ለአንድ አስፋፊ በሬሾ የሚደርሰው ሰው ብዛት አሁንም በጣም ከፍተኛ ሲሆን 10, 204 ይሆናል።
ሰዓት፦ የጉባኤ አስፋፊዎች በየወሩ በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፉት አማካይ ሰዓት ወደ 12.7 ከፍ ብሏል። በዓመቱ ውስጥ አቅኚዎችና አስፋፊዎች በድምሩ 1, 815, 654 ሰዓት በአገልግሎት ያሳለፉ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 9 በመቶ ጭማሪ አለው።
ተመላልሶ መጠይቆችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፦ በድምሩ 704, 700 ተመላልሶ መጠይቆችና በአማካይ 4, 853 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሪፖርት ተደርገዋል። ይህ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ጭማሪ ነው።
አቅኚዎች፦ በመጋቢት ወር 1, 918 የሚያህሉ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው አገልግለዋል። ይህ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ነበር። ካለፈው የመስከረም ወር ጀምሮ ከ80 የሚበልጡ አዲስ የዘወትር አቅኚዎች ተሹመዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ 200 የሚጠጉ ልዩ አቅኚዎች አሉ።
የተጠማቂዎች ቁጥር፦ 424 (ያለፈው ዓመት 398 ነበር።)
የመታሰቢያው በዓል የተሰብሳቢዎች ቁጥር 18, 595 ነበር። (ያለፈው ዓመት:- 17,728)
የመንግሥት አዳራሾች፦ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ወንድሞች ባደረጉልን እርዳታ ብዙ የመንግሥት አዳራሾች በመሠራታቸው በአሁኑ ወቅት 69 የሚያህሉ አዳራሾች አሉን። በአሁኑ ወቅት ሁለት የግንባታ ቡድኖች ያሉ ሲሆን ትጋት ለተሞላው ሥራቸው ሳናደንቃቸው አናልፍም።
ልንሠራባቸው የሚገቡ ጎኖች፦ በቅንዓትና በታማኝነት ስላከናወናችሁት አገልግሎት ከልብ እናመሰግናችኋለን። ይሖዋ ጥረታችሁን እንደባረከውና በቅርቡ የላቀ ሽልማት እንደሚጠብቃችሁ አያጠራጥርም። ለሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሰጥታችሁ በቅንዓት ማገልገላችሁን እንድትቀጥሉ እናበረታታችኋለን። (1) ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ክልሎችን መሸፈን፣ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ በመገኘት ዝግጅቱን መደገፍ። በመሠረቱ የአንድ ጉባኤ የአገልግሎት ክልሎች በዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ መሸፈን አለባቸው፤ (2) አዘውትሮ ማገልገል (1 ቆሮ. 15:58)፤ (3) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና የግል ጥናት ማድረግ (መዝ. 1:1, 2)።