ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ
1 የአምላክ ቃል “ትሑታን ሁኑ፤ ክፉን በክፉ ፈንታ . . . አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥ. 3:8, 9) ይህ ምክር የስብከቱን ሥራም በተመለከተ እንደሚሠራ አያጠያይቅም። እውነት ነው፣ ክርስቲያናዊው አገልግሎት ትሕትናችንን የሚፈትን ሊሆን ይችላል።
2 ትሕትና የሚያናድዱ ሁኔታዎችን ታግሠን እንድናልፍ የሚረዳ ባሕርይ ነው። ምሥራቹን ስንሰብክ አንዳንዶቹ ሊያመናጭቁን እንደሚችሉ ብናውቅም ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ሰዎች እናነጋግራለን። ይህን ዓይነቱን ሁኔታ ተቋቁሞ ምሥራቹን መስበክ ትሕትና ይጠይቃል። ሁለት አቅኚ እህቶች በጣም አስቸጋሪ በሆነ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጣቸው አንድም ሰው ሳያገኙ ለሁለት ዓመት ያህል ከቤት ወደ ቤት አገልግለዋል! ሆኖም በትዕግሥት ጥረት ማድረጋቸውን በመቀጠላቸው በአሁኑ ወቅት በዚያ አካባቢ ሁለት ጉባኤዎች ይገኛሉ።
3 የሚያመናጭቁ ሰዎች ሲያጋጥሙን:- የትሕትና ባሕርይ ሰዎች ሲያመናጭቁን የኢየሱስን አርዓያ እንድንኮርጅ ይረዳናል። (1 ጴጥ. 2:21-23) አንዲት እህት አንድ ቤት ስታንኳኳ መጀመሪያ ሚስትየዋ ሙልጭ አድርጋ ሰደበቻት። ባልየውም እንዲሁ ከሰደባት በኋላ ግቢውን ለቅቃ እንድትወጣ አዘዛት። እህት ፈገግ በማለት በሌላ ጊዜ ተመልሳ መጥታ ብታነጋግራቸው ደስ እንደሚላት ነገረቻቸው። ባልና ሚስቱ በእህት ምላሽ በጣም ስለተገረሙ በሌላ ጊዜ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤታቸው ስትመጣ ትኩረት ሰጥተው አዳመጧት፤ እንዲሁም በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲመጡ በመጀመሪያ ስታነጋግራቸው ያመናጨቋት እህት በሰላምታ የተቀበለቻቸው ሲሆን ተጨማሪ ምሥክርነትም ሰጠቻቸው። እኛም እንዲሁ ሰዎችን “በትሕትናና በአክብሮት” በመያዝ የተቃዋሚዎችን አመለካከት ማለዘብ እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:15 አ.መ.ት ፤ ምሳሌ 25:15
4 ሌሎችን በንቀት አትመልከቱ:- ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን እውቀት ሰዎችን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት ወይም አክብሮት በጎደለው መንገድ እንድናነጋግራቸው ምክንያት ሊሆነን አይችልም። (ዮሐ. 7:49) እንዲያውም የአምላክ ቃል ‘ማንንም እንዳንሳደብ’ ይመክረናል። (ቲቶ 3:1) ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት ልብ ካለን ለሌሎች የእረፍት ምንጭ እንሆናለን። (ማቴ. 11:28, 29) ትሕትና የተላበሰ አቀራረብ ለመልእክታችን ውበት ይጨምርለታል።
5 አዎን፣ ትሕትና በአስቸጋሪ የአገልግሎት ክልል ውስጥ በጽናት እንድንሰብክ ያስችለናል። እምቢተኛ ሰዎችን ለማለዘብ ከማስቻሉም በላይ አንዳንዶች ለምሥራቹ ጆሯቸውን እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን ‘ለትሑታን ጸጋን የሚሰጠውን’ ይሖዋን ያስደስተዋል።—1 ጴጥ. 5:5