መጨረሻው እየቀረበ በሄደ መጠን ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ
1 የይሖዋ ቀን “እንደ ሌባ” ማለትም ድንገት፣ ሳይታሰብ ከተፍ እንደሚል የአምላክ ቃል በተደጋጋሚ ይናገራል። (1 ተሰ. 5:2፤ ማቴ. 24:43፤ 2 ጴጥ. 3:10፤ ራእይ 3:3፤ 16:15) ኢየሱስም “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 24:44) መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ የሚረዳን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው “ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ” የሚለው ምክር ነው።—1 ጴጥ. 4:7 NW
2 ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ ነገሮችን በይሖዋ ዓይን መመልከትን ይጨምራል። (ኤፌ. 5:17) ይህም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ራሳችንን እንደ “እንግዶችና መጻተኞች” አድርገን እንድንመለከት ይረዳናል። (1 ጴጥ. 2:11) ከሁሉ የሚሻለው ነገር ምን እንደሆነ እንድናስተውል፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥና ጥሩ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ያስችለናል።—ፊልጵ. 1:9, 10
3 መንፈሳዊ ግቦች አውጡ:- መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ መድረስ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረን ይረዳናል። በአሁኑ ወቅት ልትደርስባቸው የምትጣጣርላቸው መንፈሳዊ ግቦች አሉህ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ፣ በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም ለማንበብ ወይም በአገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እያደረግህ ነው? ከሁኔታዎችህ ጋር የሚስማሙ ግቦችን ካወጣህ፣ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ አዘውትረህ ጥረት ካደረግህና ጥረትህን እንዲባርክልህ ይሖዋን በጸሎት ከጠየቅኸው አስደሳች ውጤት ልታገኝ ትችላለህ።
4 አንድ ሽማግሌ ለአንድ ወጣት ባልና ሚስት ስለ መንፈሳዊ ግቦቻቸው ጠየቃቸው። አኗኗራቸውን ቀላል ቢያደርጉና የኑሮ ጫና የሚያስከትሉባቸውን ዕዳዎች ቢያስወግዱ አቅኚ ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ ከጥያቄው ተገነዘቡ። በዚህ ምክንያት አቅኚነትን ግባቸው ለማድረግ ወሰኑ። በትጋት በመሥራት ዕዳቸውን ከፈሉ፤ እንዲሁም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያሟጥጡባቸውን አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ለመቀነስ እቅድ አወጡ። ልክ ከአንድ ዓመት በኋላ ግባቸው ላይ መድረስ ቻሉ። በዚህ ምን ውጤት አገኙ? ባልየው እንዲህ ይላል:- “ግብ ባናወጣ ኖሮ በፍጹም ለዚህ አንበቃም ነበር። ከበፊቱ የበለጠ ደስተኞች ነን። ሕይወታችንም የተረጋጋና ከበፊቱ የተሻለ እንዲሁም ይበልጥ ዓላማና ትርጉም ያለው ሆኖልናል።”
5 የይሖዋን ቀን በጉጉት ስንጠባበቅ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝና ሙሉ ትኩረታችንን የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ በማድረግ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንቀጥል።—ቲቶ 2:11-13