ቤትህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ቤታቸውን ለመሰብሰቢያነት በፈቃደኝነት ያቀርቡ ነበር። (1 ቆሮ. 16:19፤ ቆላ. 4:15፤ ፊልሞ. 1, 2) በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ስብሰባና የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚካሄድባቸው ቤቶች እጥረት አለ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ቡድኖች 30ና ከዚያ የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ያሏቸው ሲሆን ይህ ቁጥር አንድ መጽሐፍ ጥናት እንዲኖረው ከሚፈለገው 15 ያህል ተሰብሳቢ በጣም ይበልጣል።
2 ግሩም መብት:- ቤትህን ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሰብሰቢያነት ለማቅረብ አስበህ ታውቃለህ? ንጹሕ የሆነ፣ በቂ ብርሃንና ንጹሕ አየር ያለው ሰፊ ክፍል ለዚህ ዓላማ ተስማሚ ነው። የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማስተማር ካደረጋቸው ዝግጅቶች አንዱ ስለሆነ በቤትህ ይህ ስብሰባ መደረጉ ልዩ መብት ነው። ብዙዎች ቤታቸውን ጉባኤው እንዲጠቀምበት በመፍቀዳቸው በመንፈሳዊ በእጅጉ እንደተባረኩ ይናገራሉ።
3 ቤትህ ለዚህ ምቹ እንደሆነና ጉባኤው ሊጠቀምበት እንደሚችል ከተሰማህ ይህን ለሽማግሌዎች ንገራቸው። ተጨማሪ የመሰብሰቢያ ቦታዎች እየፈለጉ ሊሆን ይችላል። ቤትህ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ስብሰባ ማድረግ የማይቻል ከሆነ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ማድረግ ይቻል ይሆን? ለጊዜው ተጨማሪ የመሰብሰቢያ ቦታ ባያስፈልግ እንኳን ሽማግሌዎች ቤትህን ለዚህ ዓላማ መጠቀም እንደሚችሉ ማወቃቸው ጥሩ ነው። ወደፊት ይህን መብት ልታገኝ ትችል ይሆናል።
4 ጥሩ ምግባር ማሳየት:- በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ስንሰበሰብ ሁላችንም ለቤቱ ንብረት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። ወላጆች ልጆቻቸው የመጽሐፍ ጥናቱ ከሚደረግበት ክፍል ውጪ ወደ ሌሎች ክፍሎች እየገቡ አንዳንድ ነገሮችን እንዳይነካኩ መቆጣጠር ይኖርባቸዋል። እንዲሁም ጎረቤቶችን ላለመረበሽ ጥንቃቄ በማድረግ አሳቢነታችንን ማሳየት ይገባናል።—2 ቆሮ. 6:3, 4፤ 1 ጴጥ. 2:12
5 በዕብራውያን 13:16 ላይ “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ቤትህን የጉባኤ ስብሰባ እንዲደረግበት ማቅረብህ ለሌሎች መልካም ነገሮችን ለማካፈልና ‘ይሖዋን በሃብትህ ለማክበር’ የሚያስችልህ ግሩም መብት ነው።—ምሳሌ 3:9