መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የአምልኮ አንድነት በተባለው መጽሐፍ ተጠቀሙ
እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት የተባለው መጽሐፍ አዲሶች በእውነት ውስጥ እድገት እንዲያደርጉና ለይሖዋና ለድርጅቱ ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እንደ ሁለተኛ የማጥኛ መጽሐፍ አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን። የሰኔ 2000 የመንግሥት አገልግሎታችን በገጽ 4 ላይ እንደሚከተለው ይላል:- “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር እና እውቀት መጽሐፍን ካስጠናችሁ በኋላ ተማሪው በአዝጋሚ ሁኔታም ቢሆን እድገት እያደረገ እንዳለና ለሚማረው ነገር አድናቆት እያዳበረ እንደሆነ በግልጽ ከተመለከታችሁ ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍ ተጠቅማችሁ ጥናቱን ቀጥሉ። . . . ሆኖም በማናቸውም ሁኔታ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹርና እውቀት መጽሐፍ መጀመሪያ መጠናት አለባቸው። ተማሪው ሁለተኛውን መጽሐፍ አጥንቶ ከመጨረሱ በፊት ቢጠመቅም ጥናት ተብሎ ይቆጠራል። ጥናቱን ለመቀጠል የዋለው ጊዜና ተመላልሶ መጠየቅም ሪፖርት መደረግ አለበት።”
የአምልኮ አንድነት የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት ሊጠቀሙ የሚችሉ ሌሎች ሰዎች እነማን ናቸው? ከላይ የተጠቀሰው የመንግሥት አገልግሎታችን በማከል እንዲህ ይላል:- “ቀደም ሲል እውቀት መጽሐፍን ቢያጠኑም ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያበቃ እድገት እንዳላደረጉ የምታውቋቸው ሰዎች ካሉ ጥናታቸውን መቀጠል ይፈልጉ እንደሆነ ቀዳሚ ሆናችሁ ለመጠየቅ ታስቡ ይሆናል።” በመጋቢትና በሚያዝያ ወር እነዚህን ሰዎች የአምልኮ አንድነት በተባለው መጽሐፍ ጥናት ለማስጀመር ልዩ ጥረት እናድርግ።