የአካል ጉዳተኝነት ፍሬያማ ከመሆን አያግድም
1 የአካል ጉዳተኛ የሆኑ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ፤ ከእነዚህ አንዱ ከሆንክ በአገልግሎቱ ፍሬያማ መሆን ትችላለህ። እንዲያውም ያለህበት ሁኔታ ምሥክርነት ለመስጠትና ሌሎችን ለማበረታታት ጥሩ አጋጣሚ ሊከፍትልህ ይችላል።
2 ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች:- የአካል ጉዳተኛ የሆኑ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ያለባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመው በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ያደረገችው ቀዶ ሕክምና እንደልብ የመንቀሳቀስና አጥርቶ የመናገር ችሎታዋን ያሳጣት አንዲት እህት ባለቤትዋ መኪናቸውን ሰው በሚበዛበት መንገድ ዳር ካቆመው መጽሔቶች ማበርከት እንደምትችል ተመልክታለች። በአንድ ወቅት በሁለት ሰዓት ውስጥ 80 መጽሔቶች አበርክታለች! ያለህበት ሁኔታ በሌሎች ጊዜያት በቀላሉ የማይገኙ ሰዎችን ለማነጋገር አጋጣሚ ይከፍትልሃል። ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለመመሥከር ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንልህ ይችላል።
3 በስብከቱ ሥራ መካፈልህ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። ሌሎች ያለህበት ሁኔታ በአገልግሎቱ ከመካፈል እንዳላገደህና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወትህ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሲመለከቱ የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ሊነሳሱ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ችግርና መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ከራስህ ተሞክሮ በመነሳት በአምላክ ቃል ልታጽናናቸው ትችላለህ።—2 ቆሮ. 1:4
4 ሌሎችን ማበረታታት:- ለ37 ዓመታት ያህል እንደ ሳንባ ሆኖ በሚያገለግል ሰው ሠራሽ መሣሪያ ውስጥ የኖረችውና እዚያ ሆና 17 ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲያውቁ የረዳችው የሎረል ኒዝቤት ታሪክ አላበረታታህም? በተመሳሳይ የአንተ ምሳሌ የእምነት ባልንጀሮችህ በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመሥራት እንዲጥሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ጥር 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 18-21
5 ምንም እንኳን ያለህበት ሁኔታ በአገልግሎቱ የምትፈልገውን ያህል ለመካፈል ባያስችልህም ሌሎችን ልታበረታታ ትችላለህ። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ከባድ የአካል ጉዳት ያለበት ሰው እንኳ ሌሎችን ለመርዳት ብዙ ሊያደርግ እንደሚችል ተምሬያለሁ። እኔና ባለቤቴ በጉባኤ ውስጥ ለብዙዎቹ በቅርብ የምንገኝ የብርታት ምንጭ ሆነንላቸዋል። ካለብን አካላዊ እክል የተነሳ የትም ስለማንሄድ ሁልጊዜ ሊያገኙን ይችላሉ።” ሆኖም ያለህበት ሁኔታ ሁልጊዜ የምትፈልገውን ያህል እንዳታገለግል እንቅፋት ሊሆንብህ እንደሚችል ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ትንሽ ድጋፍ ቢደረግልህ በአገልግሎት ጥሩ ተሳትፎ ማድረግ ትችል ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት እርዳታ የምትፈልግ ከሆነ ጉዳዩን ለጉባኤ ሽማግሌዎች ወይም ሊረዱህ ለሚችሉ ሌሎች የጉባኤው አባላት ከመናገር ወደኋላ አትበል።
6 ይሖዋ እርሱን ለማገልገል የምታደርገውን ማንኛውንም ጥረት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ በሙሉ ነፍስ በምታቀርበው አገልግሎት ይደሰታል። (መዝ. 139:1-4) በእርሱ ከታመንህ ፍሬያማና አስደሳች አገልግሎት እንድታከናውን ኃይል ሊሰጥህ ይችላል።—2 ቆሮ. 12:7-10