የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ
1 ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ አንድ ከባድ ኃላፊነት ጥሎብናል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ።” (ማቴ. 10:11) ሰዎች በቤታቸው የሚያሳልፉት ጊዜ እያነሰ በሄደበት በዚህ ጊዜ የሚገባቸውን ሰዎች ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት ስኬታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
2 የአገልግሎት ክልላችሁን በሚገባ አጥኑት:- በክልላችሁ ውስጥ ማገልገል ከመጀመራችሁ በፊት በሚገባ አጥኑት። ሰዎች በአብዛኛው በቤታቸው የሚገኙት መቼ ነው? ቀን ቀን የት ልናገኛቸው እንችላለን? በጥሩ መንፈስ ተቀብለው ሊያነጋግሩን የሚችሉት በየትኛው የሳምንቱ ቀን ወይም ሰዓት ብንሄድ ነው? አገልግሎትህን በጉባኤው ክልል ውስጥ ካሉት ሰዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴና ሁኔታ ጋር ማስማማትህ ይበልጥ ስኬታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።—1 ቆሮ. 9:23, 26
3 በርካታ አስፋፊዎች ሰዎችን በቤታቸው ለማግኘት አመሻሹ ላይ መሄዱን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሰዓት ላይ ይበልጥ ተረጋግተው የማዳመጥ ዝንባሌ አላቸው። የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ማገልገልም ለሰዎች ምሥራቹን ማዳረስ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ናቸው። እርግጥ ነው፣ ምክንያታዊነት ከሚጎድላቸውና ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናቀርብላቸውን ማስረጃዎች ለመቀበል ከማይፈልጉ ሰዎች ጋር ፍሬ ቢስ ውይይት በማድረግ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። በተጨማሪም ለሰዎች መጽሔቶችንና መጽሐፎችን ከመስጠታችን በፊት ለማንበብ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጣችን ተገቢ ነው።
4 አንድ ጉባኤ ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚካሄድበት ወር ላይ ቅዳሜና እሁድ ከሰዓት በኋላ ረቡዕና አርብ ደግሞ አመሻሹ ላይ አስፋፊዎች አገልግሎት መውጣት የሚችሉበት ዝግጅት አደረገ። በተጨማሪም በስልክ ምሥክርነት ለመስጠትና የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ለማገልገል እቅድ አወጡ። የጉባኤው የአገልግሎት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ ጉባኤው ይህ ዝግጅት ወደፊትም እንዲቀጥል ወስኗል።
5 ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጉዎች ሁኑ:- በጉባኤያችሁ ክልል ውስጥ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ሰዎችን በቤታቸው ለማግኘት አስቸጋሪ ከሆነ በመጀመሪያው ውይይትም ሆነ በእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ ወቅት እንደገና የምትገናኙበትን ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዙ። ከዚያም ቀጠሯችሁን አክብራችሁ መሄዳችሁን አትርሱ። (ማቴ. 5:37) የሚቻል ከሆነም የቤቱ ባለቤት ስልክ ቁጥሩን እንዲሰጣችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ይህም ግለሰቡን በድጋሚ ለማግኘት ያስችላችኋል።
6 የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘትና ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትለን ለመርዳት ትጋት የተሞላበት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ እንደሚባርከን አንጠራጠርም።—ምሳሌ 21:5