የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የትዳር ጓደኞችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
1 የብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የትዳር ጓደኞች ወንድሞችንና እህቶችን የሚወዱ እንዲሁም ጉባኤ መሄድ የሚያስደስታቸው ቢሆንም የአምላክ አገልጋይ ከመሆን ወደ ኋላ ይላሉ። የአንዲት እህት ባል “ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የማገልገሉ ሐሳብ ትልቅ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። ሌሎች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ልማዶችን ማሸነፍ ይኖርባቸው ወይም የትዳር ጓደኞቻቸው በሚያደርጓቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ መካፈል እንደሚከብዳቸው ተሰምቷቸው ይሆናል። ታዲያ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
2 አሳቢነት አሳዩአቸው:- አሳቢነት ማሳየትና ምን ነገር እንደሚያሳስባቸው መገንዘብ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ መንገድ ሊከፍት ይችላል። (ፊልጵ. 2:4) ቀደም ሲል ከትዳር ጓደኛቸው የተለየ ሃይማኖት ይከተሉ የነበሩ ሰዎች ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩአቸው ፍቅራዊ አሳቢነት እንደተማረኩ ብዙውን ጊዜ ይናገራሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የማያምን ባል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ የነበረው ሆሴ ቀርቦ አነጋገረኝ። በመጨረሻም ከልቤ ጥናት እንድጀምር ያነሳሳኝ የእርሱ ማበረታቻ ይመስለኛል።” የአንዲት እህት ባል ደግሞ እቤት እየመጡ የሚጠይቋቸው ወንድሞች እርሱ ስለሚወዳቸው ነገሮች እያነሱ ያጫውቱት እንደነበር ተናግሯል። እንዲህ ብሏል:- “[የባለቤቴን] እምነት ፍጹም በተለየ መልኩ እመለከተው ጀመር። ጓደኞቿ ስለ ተለያዩ ጉዳዮች አንስተው መናገር የሚችሉ በጣም አዋቂ ሰዎች ነበሩ።”—1 ቆሮ. 9:20-23
3 ተግባራዊ እርዳታ ስጡ:- በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የትዳር ጓደኞች በደግነት በሚደረግላቸው መልካም ነገር ልባቸው ይነካ ይሆናል። (ምሳሌ 3:27፤ ገላ. 6:10) አንድ የማያምን ባል መኪናው ተበላሽቶበት አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በመጠገኑ ሥራ ስለረዳው “ይህ በጣም ነካኝ” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። የአንዲት እህት የማያምን ባል የግቢውን አጥር በሚያጥርበት ጊዜ አንድ ሌላ ወንድም ሙሉ ቀን በሥራው ረዳው። አብረው እያወሩ ሲሠሩ ይበልጥ ተግባቡ። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰውየው ወደ ወንድም ቀርቦ እንዲህ አለው:- “በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርብኝ ተገንዝቤያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናኝ ትችላለህ?” ይህ ሰው ፈጣን እድገት ያደረገ ሲሆን አሁን የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።
4 በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ከመፈለጉ ሥራ ጎን ለጎን የክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን የማያምኑ የትዳር ጓደኞች መርዳታችንንም እንቀጥል።—1 ጢሞ. 2:1-4