ይሖዋ የሚፈልግብንን ማሟላት እንችላለን
1. አንዳንድ ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል? ለምንስ?
1 ከይሖዋ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር በጊዜያችን የተሻለ ሕይወት እንድንመራ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ለዘላለም ሕይወት ጽኑ መሠረት እንድንጥል ይረዳናል። (መዝ. 19:7-11፤ 1 ጢሞ. 6:19) ይሁን እንጂ የሰይጣን ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ ፈታኝ ያደርግብናል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻችንን ለመወጣት ስንጥር አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማን ይችላል። (መዝ. 40:12፤ 55:1-8) እንዲያውም ይሖዋ የሚፈልግብንን ሁሉ ማሟላት መቻላችንን መጠራጠር እንጀምር ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን መንፈሳዊ ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?
2. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር በሚመለከት ምክንያታዊ የሆነው እንዴት ነው?
2 የይሖዋ ትእዛዛት ከባዶች አይደሉም፦ ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ሸክም አይጭንብንም። ትእዛዛቱ ለእኛው ጥቅም የሚያስገኙ እንጂ ከባዶች አይደሉም። (ዘዳ. 10:12, 13፤ 1 ዮሐ. 5:3) ‘ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስብ’ ሰብዓዊ ድክመቶቻችንን ግምት ውስጥ ያስገባል። (መዝ. 103:13, 14) ያለንበት ሁኔታ እርሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት የሚገድብብን ቢሆንም እንኳን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ የምንጥር ከሆነ አምላክ ይደሰትብናል። (ዘሌ. 5:7, 11፤ ማር. 14:8) ሸክማችንን በእርሱ ላይ እንድንጥል ግብዣ ያቀረበልን ሲሆን በታማኝነት ጸንተን እንድንቀጥል እንደሚረዳን ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መዝ. 55:22፤ 1 ቆሮ. 10:13
3. ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችለንን ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው?
3 የጽናት አስፈላጊነት፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኤልያስ፣ ኤርምያስ እና ጳውሎስ ስላሉት እስከ መጨረሻው በታማኝነት የጸኑ የአምላክ አገልጋዮች የሚናገረው ታሪክ የመጽናትን አስፈላጊነት ያጎላል። (ዕብ. 10:36) መከራና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ባጋጠሟቸው ጊዜያት ይሖዋ ረድቷቸዋል። (1 ነገ. 19:14-18፤ ኤር. 20:7-11፤ 2 ቆሮ. 1:8-11) እንዲሁም በጊዜያችን ያሉ ወንድሞቻችን የሚያሳዩት ታማኝነት እስከ መጨረሻው እንድንጸና ያበረታታናል። (1 ጴጥ. 5:9) እንደ እነዚህ ባሉ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።
4. አምላክ የገባልንን ተስፋ ሕያው አድርገን በልባችን መያዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 አምላክ በገባልን ቃል ላይ ያለን ተስፋ “የነፍስ መልሕቅ” ነው። (ዕብ. 6:19) አብርሃምና ሣራ ቤታቸውን ትተው ‘በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋይቱ ምድር እንዲቀመጡ’ አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው እንዲህ ያለው ተስፋ ነው። ሙሴም ለእውነተኛው አምልኮ በድፍረት እንዲሟገት ኃይል የሰጠው ይኸው ተስፋ ነው። ኢየሱስም በመከራ እንጨት ላይ ለመጽናት እንዲችል አጠንክሮታል። (ዕብ. 11:8-10, 13, 24-26፤ 12:2, 3) አምላክ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት የገባልንን ቃል በልባችን ሕያው አድርገን መያዛችንም እስከመጨረሻው ጸንተን እንድንኖር ሊረዳን ይችላል።—2 ጴጥ. 3:11-13
5. በታማኝነት ያሳለፍናቸውን ዓመታት ማስታወሳችን የሚያበረታታን እንዴት ነው?
5 በታማኝነት፣ የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግና በድፍረት በማገልገል ያሳለፍናቸውን ዓመታት መለስ ብለን ማስታወሳችንም ለአገልግሎት ብርታት ሊጨምርልን ይችላል። (ዕብ. 10:32-34) እንዲሁም ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገውን በሙሉ ልብ የሚቀርብ አምልኮ በመስጠታችን ያገኘነውን ደስታ ያስታውሰናል።—ማቴ. 22:37