መላእክት እየረዱን ነው
1 “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ኢየሱስ ‘ስለዚህ ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ለሚያደርጉ ሁሉ ከላይ ያለው ጥቅስ በጣም የሚያበረታታ ነው! (ማቴ. 28:18-20) ኢየሱስ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር የሚሆንበት አንዱ መንገድ በመላእክቱ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 13:36-43) ከእነዚህ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር በመሆን ‘የዘላለምን ወንጌል’ ማወጅ ምንኛ አስደሳች ነው!—ራእይ 14:6, 7
2 በአገልግሎታችን፦ መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት “መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ” እንደሆኑ ይገልጻል። (ዕብ. 1:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ተከታዮች ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች እንዲያነጋግሩ በመርዳት ረገድ መላእክት ድርሻ ነበራቸው። (ሥራ 8:26) ዛሬም መላእክት የአምላክ አገልጋዮችን እንደሚመሯቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የሰዎችን ቤት ሲያንኳኩ የቤቱ ባለቤቶች እርዳታ ለማግኘት እየጸለዩ እንደነበረ የተናገሩባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሰምተው ምላሽ ሲሰጡ እኛም ሆንን መላእክት በጣም እንደሰታለን!—ሉቃስ 15:10
3 ተቃውሞ ሲያጋጥመን፦ ይሖዋ ከባድ ፈተና ላጋጠማቸው እንደ ዳንኤል፣ ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ ላሉት በርካታ አገልጋዮቹ ‘በኀያላን’ መላእክቱ አማካኝነት ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (መዝ. 103:20፤ ዳን. 3:28፤ 6:21, 22፤ ሥራ 12:11) ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ረዳት እንደሌለን ሊሰማን ቢችልም “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት [እንደሚበልጡ]” ከተገነዘበው ከኤልሳዕ አገልጋይ ተሞክሮ ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን። (2 ነገ. 6:15-17) ከክርስቲያን ወንድሞቻችን እንድንለይ የሚያስገድደን ሁኔታ ቢያጋጥመን እንኳ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። የአምላክ ቃል “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መዝ. 34:7
4 በቅርቡ የመላእክት ሠራዊት የክርስቶስን ንግሥና የሚቃወሙትን ሁሉ ለማጥፋት ግልቢያ ይጀምራሉ። (ራእይ 19:11, 14-15) ያንን ቀን እየተጠባበቅን በክርስቶስ አመራር ሥር ያለው በሰማይ የሚገኝ ሠራዊት ድጋፍ እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ሆነን ይሖዋን በድፍረት ማወደሳችንን እንቀጥል።—1 ጴጥ. 3:22