የይሖዋን ሥልጣን ማክበር አለብን
ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን የተባሉትን በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች ስም ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ‘ዓመጸኛ መሆናቸው’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። በማን ላይ ነበር ያመጹት? በመለኮታዊ ሥልጣን ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች ስለተከተሉት መጥፎ አካሄድ የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ በዘኍልቁ ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኝ ሲሆን በነሐሴ 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ ደግሞ “ለመለኮታዊ ሥልጣን በታማኝነት ተገዙ” በሚል የጥናት ርዕስ የታሪኩ ዋና ዋና ገጽታዎች ተብራርተዋል። ይህንን ትምህርት ብታነብና ከዚያም ትኩረት በሚስብ መልክ የተዘጋጀውን የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ የተሰኘውን የቪዲዮ ፊልም ብትመለከት ትጠቀማለህ። ታማኝ በሆኑት የቆሬ ልጆችና ከአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ጋር በተጋጨው ዓመጸኛ አባታቸው መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ትመለከታለህ። (ዘኍ. 26:9-11) በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተው ይህ ድራማ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ይበልጥ እንድናጠነክር ሊያበረታታን ይገባል።
ይህንን የቪዲዮ ፊልም ስትመለከት ቆሬና ግብረ አበሮቹ ታማኝ ሳይሆኑ የቀሩባቸውን ስድስት አቅጣጫዎች ለማስተዋል ሞክር:- (1) ለመለኮታዊ ሥልጣን አክብሮት እንደጎደላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (2) ኩራት፣ የሥልጣን ጥምና ቅናት እንደተጠናወታቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? (3) ይሖዋ በሾማቸው ሰዎች ጉድለቶች ላይ ያተኮሩት እንዴት ነው? (4) የአጉረምራሚነት መንፈስ እንዳላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? (5) ባላቸው የአገልግሎት መብት ያልረኩት ለምን ነበር? (6) ለአምላክ ሊያሳዩ ከሚገባው ታማኝነት ይልቅ ወዳጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያስቀደሙት እንዴት ነው?
ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ ያገኘነው ትምህርት ዛሬ ለመለኮታዊ ሥልጣን ባለን አመለካከት ረገድ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል እንመልከት:- (1) የጉባኤ ሽማግሌዎች ለሚያደርጉት ውሳኔ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ? (2) በውስጣችን ተገቢ ያልሆነ ምኞት እንዳያድር መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? (3) አመራር እንዲሰጡ የተሾሙት ወንድሞች ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ለሚፈጽሟቸው ስህተቶች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (4) በውስጣችን የአጉረምራሚነት መንፈስ ማቆጥቆጥ ቢጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል? (5) የተሰጡንን የአገልግሎት መብቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? (6) ለአምላክ ከምናሳየው ታማኝነት እነማንን ማስቀደም የለብንም? እንዲህ ማድረግ ከባድ ፈተና የሚሆንብን ምን ጊዜ ነው?
ይህ ትምህርት በጉባኤ ከቀረበ በኋላ የቪዲዮ ፊልሙን ለምን በድጋሚ አትመለከተውም? እንዲህ ማድረግህ የይሖዋን ሥልጣን ምንጊዜም ማክበር የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ በማይፋቅ ሁኔታ በአእምሮህ ለመቅረጽ ያስችልሃል።—መዝ. 18:25፤ 37:28