የይሖዋን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል አዲስ ቤቴል
በኢትዮጵያ ያለው ቤቴል በ1953 በጊዜው ለነበሩት ሃያ የሚያህሉ አስፋፊዎች የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በቸርችል ጎዳና አጠገብ በኪራይ ቤት ውስጥ ከተቋቋመው የመጀመሪያው ትንሽ ቅርንጫፍ ቢሮ ተነስቶ አሁን የደረሰበት ደረጃ ሲታይ በእርግጥም ትልቅ እርምጃ ነው ለማለት ይቻላል። በዚያን ጊዜ የተቋቋመው ቢሮ ከአራት ዓመታት በኋላ ተዘግቶ ነበር። ከአሥር ዓመት በፊት ደግሞ በቦሌ የቁጠባ ቤቶች ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤት በድጋሚ የቅርንጫፍ ቢሮ የተቋቋመ ሲሆን ይህ ቢሮ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ሄዶ ስምንት የሚያህሉ የኪራይ ቤቶችን የሚያጠቃልል ሆኖ ነበር። ይህ በሥራው ላይ ራሱን የቻለ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው። ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ ግን 70 የሚያህሉ አባላት ያሉት የቤቴል ቤተሰባችን ከታች በሥዕሉ ላይ ወደሚታየው ከኮተቤ የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ በስተ ምሥራቅ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ያማረ ሕንጻ በመዛወሩ የእናንተንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመስኩን ፍላጎት ለማሟላት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል። አሁን በይሖዋ ሥራ ላይ ከበፊቱ የበለጠ ጊዜና ጉልበት ማዋል የሚቻል ሲሆን ይህም ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። በቅርንጫፍ ቢሮው ግቢ ውስጥ የሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወደ 2,000 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎችን መያዝ የሚችል ሲሆን በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ከቲኦክራሲያዊው ትምህርት ለመካፈል የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። አዳራሹ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ፣ ምቹ አግዳሚ ወንበሮች፣ ከመድረኩ ጋር ተያይዞ የተሠራ የጥምቀት ገንዳና በቂ የመጸዳጃ ቤቶች ያሉት ከመሆኑም በላይ በቀላሉ መግባትና መውጣት እንዲቻል ዙሪያውን ክፍት ሆኖ የተሠራ ነው። በእጅጉ ያስፈልጉን የነበሩትን እነዚህን ሕንጻዎች ስለሰጠን ሊወደስ የሚገባው ይሖዋ በመሆኑ ከልባችን እናመሰግነዋለን።—ዘካ. 4:6
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅርንጫፍ ቢሮው ከፊት ለፊት ሲታይ
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቅርንጫፍ ቢሮው በስተጀርባ የሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ እና የመሰብሰቢያ አዳራሽ