ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ሥራዎች በፈቃደኝነት ትሠራለህ?
1 ትሕትና የአምላክን ሞገስ ያስገኝልናል። መዝሙር 138:6 ስለ ይሖዋ ሲናገር “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል” ይላል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የትሕትና ባሕርይ የሚጎድላቸው ሲሆን ከበሬታ ማግኘትን፣ ታዋቂ መሆንንና ሥልጣንን ይፈልጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በላከው ደብዳቤ ላይ የሚከተለውን ምክር ሰጥቶ ነበር:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) አክሎም “የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” በማለት ወንድሞቹን መክሯቸዋል። የአዲሱ መደበኛ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ የመጨረሻውን ሐረግ “ዝቅተኛ ሥራ ለመሥራት ፍቀዱ” በማለት ተርጉሞታል።—ሮሜ 12:3, 16 የ1954 ትርጉም
2 እኛስ ዝቅተኛ የሚባሉ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኞች ነን? ወይስ በሌሎች ዘንድ “ታዋቂ” እንደሚያደርጓቸው የሚያስቧቸውን ወይም ችሎታቸውን የሚፈትኑ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ ሆነው ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ ሲጠየቁ ግን ቅር እንደሚላቸው በርካታ ሰዎች ነን?
3 አንዳንድ ዝቅተኛ የሚባሉ ሥራዎች ተፈጥሯዊ ግዴታ ከመሆናቸውም በላይ የዕለት ተዕለት ሕይወት ክፍል ናቸው። ልጆች የወላጆቻቸውን ትእዛዝ የሚፈጽሙና የተሰጣቸውን ማንኛውንም የቤት ውስጥ ሥራ የሚያከናውኑ ከሆነ የአምላክን ሞገስ ከማግኘታቸውም በላይ ወላጆቻቸው ይወዷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ ‘መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም’ የሚል ነው።”—ኤፌ. 6:1-3
4 ብዙውን ጊዜ ሚስቶች ግሩም የትሕትና ባሕርይ በማሳየት ረገድ ምሳሌ ይሆናሉ። አብዛኛው ሥራቸው ከቤት ወጥቶ ለሰዎች የሚታይ አይደለም። አንዲት የቤት እመቤት ከምታከናውነው ሥራ ውስጥ አብዛኛው ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን ዘመን አመጣሽ የሆነው አስተሳሰብ ደግሞ ብዙም ጠቀሜታ እንደሌለው አድርጎ በመቁጠር አቃልሎ ይመለከተዋል። ሆኖም ይህ ሥራ ለቤተሰቡ ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከዚህም በላይ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሚስቶች “ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ” እና ይህን ፍቅራቸውን “በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮች፣ ለባሎቻቸው የሚገዙ” በመሆን እንዲያሳዩ የሚያበረታታውን ይሖዋንም ያስደስተዋል። (ቲቶ 2:4, 5) አዎን፣ አምላክ ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን በትጋት የሚንከባከቡና የቤት ውስጥ ሥራዎቻቸውን በጥንቃቄ የሚያከናውኑ ክርስቲያን ሚስቶችንና እናቶችን በአድናቆት ይመለከታቸዋል። የሚያከናውኑትን መልካም ተግባር የሚያስተውለው ከመሆኑም በላይ ትልቅ ግምት እንደሚሰጠው የተከበረ ሥራ አድርጎ ይመለከተዋል።—ከምሳሌ 31:10-31 ጋር አወዳድር
5 ዓለም ክብርና ዝና ያስገኛሉ ለሚባሉና በአንጻሩ ደግሞ ዝቅተኛ ተደርገው ለሚታዩ ወይም ‘ክብር ይቀንሳሉ’ ለሚባሉ ሥራዎች ያለው አመለካከት ከእውነታው የራቀና ሙሉ በሙሉ የተገላቢጦሽ ነው። ይህ ዓለማዊ አመለካከት ከራሱ ከሥራው በማይተናነስ ወይም በበለጠ ሁኔታ ትሕትናን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል።
6 በክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ትሑት መሆን እንደሚያስፈልግ ሁሉ በክርስቲያን ጉባኤ ሥር በታቀፈው ‘የወንድማማች ማኅበር’ ውስጥም የትሕትና ባሕርይ ማስፈለጉ የማይቀር ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጐልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥ. 5:5
7 በጉባኤው ውስጥ ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ወጣቶች የጉባኤ ሽማግሌዎች ሊኖራቸው የሚገባውን ተሞክሮና እውቀት ማካበት እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ከመመልከት ይልቅ ‘ዝቅተኛ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞች’ ይሆናሉ።—ሮሜ 12:3, 16 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሥራ 19:22፤ 2 ጢሞ. 4:11
8 በጉባኤ ውስጥ እምብዛም ከዓይን የማይገቡ ወይም ታዋቂ የማያደርጉ በርካታ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች አሉ። የጽዳት ወይም ሌላ ዓይነት የጉልበት ሥራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ዓይነቶቹ ሥራዎች ብዙም ከዓይን የማይገቡ መሆናቸውን ተመልክተው በእነዚህ ሥራዎች ከመካፈል ወደኋላ አይሉም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቶቹን ሥራዎች በፈቃደኝነት የሚሠሩ ከሆነ በአምላክና ትክክለኛ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ክብርና አድናቆት ያተርፋሉ። ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ ‘መሠራት ያለበት ሥራ አለ? ካለስ ይህን ሥራ በመሥራት ሌሎችን መጥቀም እችላለሁ?’ የሚለው ብቻ መሆን አለበት። ይህ በራሱ በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ በፈቃደኝነትና በደስታ እንድንካፈል የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት ነው።
9 ሁሉም ‘እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ሲለብስ’ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነው! ሁላችንም ኩራትን አስወግደን አንዳችን ሌላውን በደስታና በፈቃደኝነት የምናገለግል ከሆነ ሁሉም ሰው በዓለም መሥፈርት ሳይሆን ከአምላክ ቃል አኳያ ተመዝኖ ተገቢው ክብር ስለሚሰጠውና ዋጋ እንዳለው ስለሚሰማው ከልብ ይደሰታል።—1 ጴጥ. 5:5፤ መዝ. 133:1፤ ሮሜ 12:10
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ሥራዎች በፈቃደኝነት ትሠራለህ?
(ከገጽ 8 የዞረ)
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(ወደ ገጽ 7 ዓምድ 2 ዞሯል)