ክፍል 6—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ጥናቶቻችን ጥያቄ ሲያነሱ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
1 መደበኛ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ከጀመርን በኋላ የተለያዩ ርዕሶችን እያነሱ ከመወያየት ይልቅ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ጥናቱን መምራት የተሻለ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ተማሪው ለሚያገኘው ትክክለኛ እውቀት ጽኑ መሠረት እንዲኖረውና መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ያስችለዋል። (ቆላ. 1:9, 10) ብዙውን ጊዜ ተማሪው በጥናቱ ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ያነሳል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2 አስተዋይ ሁን፦ ተማሪው እየተጠና ባለው ክፍል ላይ ጥያቄ ካነሳ አብዛኛውን ጊዜ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት ይቻላል። የጠየቀው ጥያቄ መልስ የሚያጠናው ጽሑፍ ላይ ቢኖርም ገና አልደረስንበት ከሆነ ወደፊት በጥናቱ ወቅት ሊመለስለት እንደሚችል መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። ሆኖም የተነሳው ጥያቄ ከምንወያይበት ርዕስ ጋር ምንም ግንኙነት ከሌለው ወይም ደግሞ ጥሩ መልስ ለመስጠት ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንዳለብን ከተሰማን ከጥናቱ በኋላ ካልሆነም ሌላ ጊዜ መድበን ማወያየት ይኖርብናል። አንዳንድ አስፋፊዎች ጥያቄውን ወዲያውኑ በማስታወሻቸው ላይ ያሰፍሩታል። ይህም አስጠኚው ተማሪው የጠየቀውን ጥያቄ በቁም ነገር እንደያዘው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በጥናቱ ወቅት ትኩረታቸው ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይወሰድ ያደርጋል።
3 ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ጥናት ለመምራት በምንጠቀምባቸው ጽሑፎች ላይ የተብራሩት በአጭሩ ነው። ጥናታችን አንዳንድ ትምህርቶችን አምኖ መቀበል ቢያዳግተው ወይም አንድን የሐሰት ትምህርት መተው ቢከብደውስ? እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል በጥልቀት የሚያብራሩ ጽሑፎችን ተጠቅሞ ተጨማሪ ውይይት ማድረጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ካደረግንም በኋላ ተማሪው በቀረቡት ማስረጃዎች ማመን ካልቻለ ግን ጉዳዩን ለሌላ ጊዜ በማቆየት መደበኛ የሆነውን ጥናታችንን መቀጠል ይኖርብናል። (ዮሐ. 16:12) መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀቱ ይበልጥ እየሰፋ ሲሄድና መንፈሳዊ እድገት ሲያደርግ ለማመን አስቸጋሪ ሆኖበት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መረዳት ይችል ይሆናል።
4 ትሑት ሁን፦ ለተነሳው ጥያቄ በእርግጠኝነት ምላሽ መስጠት የማትችል ከሆነ የራስህን አስተያየት ለመስጠት አትድፈር። (2 ጢሞ. 2:15፤ 1 ጴጥ. 4:11) በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር በማድረግ መልሱን ይዘህ እንደምትመጣ መግለጽ ይኖርብሃል። እንዲያውም ይህን ዓይነቱን አጋጣሚ ጥናትህ ምርምር ማድረግ እንዴት እንደሚችል ለማሳየት ልትጠቀምበት ትችላለህ። በይሖዋ ድርጅት የተዘጋጁትን የተለያዩ የምርምር መሣሪያዎች እንዴት መጠቀም እንደሚችል በሂደት ልታሳየው ይገባል። ከጊዜ በኋላ ጥናትህ ለጥያቄዎቹ ራሱ መልሶችን ፈልጎ ማግኘት ይለምዳል።—ሥራ 17:11