የአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውሰና—ታሪካዊ ዕለት
ኅዳር 20 የተደረገው የቅርንጫፍ ቢሮ ውሰና በኢትዮጵያ ለሚከናወነው የይሖዋ ሥራ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር ለማለት ይቻላል። በዚህ አስደሳች ዕለት ማለትም ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ “ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጣ መስፋፋት” በሚል ርዕስ የውሰና ንግግር አቀረበ። በቤቴል ግቢ ውስጥ በስተ ጀርባ በሚገኘው ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀረበው በዚህ ንግግር ላይ 2,230 የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በዚህ የውሰና ፕሮግራም ላይ ከ29 አገሮች የመጡ ወደ 200 የሚጠጉ እንግዶች ተገኝተዋል። እነዚህ እንግዶች በስተ ምሥራቅ እንደ ጃፓንና ኮሪያ፣ በስተ ሰሜን እንደ ኖርዌይና ካናዳ፣ በስተ ምዕራብ እንደ ሜክሲኮና ካሊፎርኒያ በስተ ደቡብ ደግሞ እንደ አውስትራሊያና ደቡብ አፍሪካ ከመሳሰሉ አገሮች የመጡ ናቸው። ከዚህም በላይ ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ጨምሮ ከተጠመቁ 15 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንድሞችና እህቶች በውሰናው ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር።
ከውሰናው በፊት በፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡትን ክፍሎች፣ የፕሮግራሙን ብሮሹር፣ በደረት ላይ የሚለጠፉ ካርዶችን፣ እንግዶች የሚያርፉባቸውን ቦታዎች፣ ከአውሮፕላን ማረፊያ የሚመጡበትን መንገድ፣ የመረጃ ዴስክ፣ የቤቴል አስጎብኚዎችን፣ ምግብና ሌሎች በርካታ ነገሮችን በማቀናጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በተጨማሪም ከውጭ የመጡ ብዙ እንግዶች ውብ የሆኑ የአገሪቱን ገጠራማ ክፍሎች እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል።
ቅዳሜ ጠዋት፣ ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በግሩም ሁኔታ የተገነባውን የቤቴል ቤትና ቅርንጫፍ ቢሮ በመጎብኘታቸው ደስታቸው ወሰን አልነበረውም። ቀለል ያለ ምሳ ከተበላ በኋላ ከሰዓት በኋላ የውሰናው ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን ዝግጅቱ እስከ ምሽት ድረስ የዘለቀ ነበር። በውሰናው ፕሮግራም ላይ የሌሎች አገሮች ሪፖርት ቀርቦ ነበር። ለምሳሌ ያህል በቡሩንዲ በገለልተኛ ቡድን ውስጥ የሚያገለግል አንድ ወንድም የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን ለማድረስ ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ በእግሩ እንደተጓዘ ተነግሯል። በቡሩንዲ የእርስ በርስ ጦርነቱ አሁን ድረስ ባልበረደባቸው አስቸጋሪ አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች በየወሩ በአማካይ 17 ሰዓት ያገለግላሉ! በሱዳን ወንድሞች 19 የመንግሥት አዳራሾች ከመገንባታቸውም በተጨማሪ 6,000 የሚያክሉ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያን ቲኦክራሲያዊ ታሪክ የዳሰሰው ንግግር የብዙዎችን ስሜት የነካ ነበር። በዚህ ንግግር ላይ በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ሚስዮናውያን መካከል በ1950ዎቹ፣ ለአምስት ዓመታት ያህል በአገሪቱ ውስጥ ካገለገለች አንዲት እህት ጋር ቃለ ምልልስ ተደርጓል። ብርቱ ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ ከአቋማቸው ፍንክች ባለማለት ግሩም ምሳሌ ለሆኑ ወንድሞችና እህቶችም ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። የግንባታውን ሒደት አስመልክቶ በቀረበው ክፍል ላይ ለግንባታው የሚሆን ቦታ ለማግኘት፣ ለመግዛትና አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በርካታ መሰናክሎች አጋጥመው እንደነበር ተወስቷል። ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ገንዘብ የተገኘው ከአራት አህጉራት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ይህም የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት እንዳላቸው የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው። ከመላው ዓለም የተላከው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በርካታ ከመሆኑ የተነሳ የግለሰቦቹንና የአገሮቹን ስም ብቻ መጥራት የግድ ሆኖ ነበር።
በማግሥቱ ማለትም እሁድ ዕለት ጠዋት በአዲስ አበባ ስታዲየም 7,232 ተሰብሳቢዎች በተገኙበት የውሰናው ፕሮግራም ፍሬ ሐሳብ ቀረበ። ከዚያም ወንድም ሎሽ እውነተኛ ሀብትን በሚመለከትና በዚህ ዓለም ከፍተኛ ትምህርት መከታተልን አስመልክቶ ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ የሚገልጽ ንግግር አቅርቧል። በቦታው የተገኙት ሁሉ ለይሖዋ በረከት በአመስጋኝነት ስሜት የተሞሉ ከመሆኑም በላይ የቀረውን ጊዜ በአደራ የተሰጠንን አስፈላጊ ሥራ በመሥራት ነቅቶ ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት አጠናክረዋል።—1 ቆሮ. 15:58