የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ክፍል 10፦ ጥናቶቻችን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት እንዲካፈሉ ማሠልጠን
1 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን እንዳሟላ ሽማግሌዎች ሲወስኑ ግለሰቡ ከጉባኤው ጋር ሆኖ በስብከቱ ሥራ ሊሳተፍ ይችላል። (የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 79-81 ተመልከት።) ጥናቱን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት እንዲካፈል እንዴት ልንረዳው እንችላለን?
2 አብሮ መዘጋጀት:- ጥሩ ዝግጅት በጣም አስፈላጊ ነው። ለጥናቱ የናሙና አቀራረቦችን ከመንግሥት አገልግሎታችን እና ከማመራመር መጽሐፍ ሊያገኝ እንደሚችል ካሳየኸው በኋላ ለክልሉ ተስማሚ የሆነ ቀለል ያለ መግቢያ እንዲመርጥ እርዳው። ገና ከጅምሩ አገልግሎቱን ሲያከናውን በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲጠቀም አበረታታው።—2 ጢሞ. 4:2
3 አብሮ መለማመድ ለአዲስ አስፋፊ በጣም ጠቃሚ ነው። ጥናቱ መግቢያውን እየተለማመደ እያለ በክልሉ ውስጥ ሰዎች በአብዛኛው ለሚሰነዝሯቸው ሐሳቦች እንዴት በጥበብ መልስ መስጠት እንደሚችል አሳየው። (ቈላ. 4:6) አንድ ክርስቲያን የቤቱ ባለቤት ለሚያነሳው ጥያቄ ሁሉ መልስ ማወቅ እንደማያስፈልገው ንገረው። ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ የመሰሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ምርምር አድርጎ በሌላ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ሐሳብ ማቅረቡ የተሻለ ይሆናል።—ምሳሌ 15:28
4 አብሮ ማገልገል:- ጥናቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል አብራችሁ ሆናችሁ የተዘጋጃችሁትን መግቢያ ስትጠቀምበት እንዲመለከት አድርግ። ከዚያም በውይይቱ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ አድርግ። አንዳንድ ጊዜ አዲሱ አስፋፊ አንድ ጥቅስ እንዲያነብና በጥቅሱ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ ብቻ ማድረጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። የጥናትህን ባሕርይና ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። (ፊልጵ. 4:5 NW ) ደረጃ በደረጃ በስብከቱ ሥራ የተለያዩ ዘርፎች እንዲካፈል ስታሰለጥነው ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ አመስግነው።
5 አዲሱ አስፋፊ ከተቻለ በየሳምንቱ በአገልግሎት የሚሳተፍበት ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖረው መርዳት አስፈላጊ ነው። (ፊልጵ. 3:16) አብራችሁ የምታገለግሉበት የተወሰነ ጊዜ መመደብ እንዲሁም ከሌሎች ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሮ እንዲሠራ ማበረታታት ያስፈልጋል። የእነርሱን ፈለግ መከተሉና አብሯቸው ማገልገሉ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት ደስታ እንዲያገኝና ችሎታውን እንዲያሻሽል ይረዳዋል።