ክፍል 12፦ ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያስጀምሩና እንዲመሩ መርዳት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
1 በአገልግሎት መካፈል ለጀመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ጥናት የማስጀመሩና የመምራቱ ሐሳብ የፍርሃት ስሜት ያሳድርባቸው ይሆናል። ታዲያ አስፈላጊ ለሆነው ለዚህ የአገልግሎት ዘርፍ አዎንታዊ አመለካከት እንዲይዙ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን ካሟላ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀመ መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም ክፍል ሲሰጠው እንዴት እንደሚዘጋጅና እንደሚያቀርብ ያገኘው ሥልጠና ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ ጠቃሚ የሆነውን የማስተማር ክህሎት ለማዳበር ይረዳዋል፤ እንዲሁም ‘የማያሳፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ’ እንዲሆን ያስችለዋል።—2 ጢሞ. 2:15
3 ምሳሌ በመሆን አስተምሩ:- ኢየሱስ ግልጽ የሆነ መመሪያ በመስጠትና መልካም አርዓያ በመሆን ደቀ መዛሙርቱን አሠልጥኗቸዋል። “በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል” በማለትም ተናግሯል። (ሉቃስ 6:40) ልክ እንደ ኢየሱስ አንተም በምታከናውነው አገልግሎት ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆንህ በጣም አስፈላጊ ነው። ጥናትህ በአገልግሎት ላይ የምታደርገውን ትጋት የታከለበት እንቅስቃሴ ማየቱ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መሆኑን እንዲገነዘብ ይረዳዋል።
4 ጥናት እንዲጀምሩ ሰዎችን ስንጋብዝ ስለ አጠናኑ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ መስጠት ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ለጥናትህ ግለጽለት። ብዙውን ጊዜ ከሚጠናው ጽሑፍ ላይ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን ተጠቅሞ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ማሳየቱ ብቻ በቂ ነው። ይህን ለማድረግ የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን በዚሁ እትም ገጽ 8 ላይ አሊያም በጥር 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6 ላይ ታገኛለህ።
5 አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥናትህ በአንተ ወይም ተሞክሮ ባለው ሌላ አስፋፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ላይ እንዲገኝ አድርግ። በዚህ ጊዜ በአንድ አንቀጽ ወይም ቁልፍ ጥቅስ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል። ተማሪው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጥናቶች እድገት እንዲያደርጉ እንዴት መርዳት እንደሚቻል ብዙ ትምህርት ያገኛል። (ምሳሌ 27:17፤ 2 ጢሞ. 2:2) ላደረገው ጥረት ጥናትህን አመስግነው እንዲሁም ማሻሻያዎችን እንዴት ማድረግ እንደሚችል አወያየው።
6 አዲስ አስፋፊዎች የአምላክ ቃል አስተማሪ እንዲሆኑ ማሠልጠን “ለመልካም ሥራ” ያስታጥቃቸዋል፤ ይህ መልካም ሥራ የራሳቸውን ጥናት ማስጀመርንና መምራትን ይጨምራል። (2 ጢሞ. 3:17) ከእነርሱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን “የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ” የሚለውን ፍቅራዊ ግብዣ ለሌሎች ማድረስ እንዴት ያስደስታል!—ራእይ 22:17