“መዳናችን ቀርቧል” የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
1. ጥንት የአምላክ ሕዝቦች ለእውነተኛው አምልኮ ያላቸውን አድናቆት የገለጹት እንዴት ነበር? በዛሬው ጊዜስ ምን ተመሳሳይ አጋጣሚ ተከፍቶልናል?
1 የጥንቷ ይሁዳ ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስ እስራኤላውያን በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የሚጋብዙ ደብዳቤዎችን የያዙ መልእክተኞችን ልኮ ነበር። (2 ዜና 30:6, 13) የሕዝቡ ምላሽ ለእውነተኛው አምልኮ ያላቸውን አመለካከት ያሳይ ነበር። (2 ዜና 30:10-12) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችም በቀጣዮቹ ወራት፣ በአንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ለማምለክ ላገኙት መብት ያላቸውን ልባዊ አድናቆት የሚያሳዩበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። “መዳናችን ቀርቧል!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድትገኙ የሚጋብዝ ደብዳቤ ለየጉባኤያችሁ ተልኳል። ለዚህ ግብዣ ምን ምላሽ ትሰጡ ይሆን?
2. ከአውራጃ ስብሰባው ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ከአሁኑ ምን ማድረግ እንችላለን?
2 ከወዲሁ ዝግጅት አድርጉ፦ በፍቅራዊ መንገድ ከተዘጋጀው መንፈሳዊ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ከፈለግን ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ በስብሰባው ላይ መገኘት ይኖርብናል። እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ በሦስቱም ቀን እንድትገኙ ከአሁኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋችሁን መጀመራችሁ ጥበብ ነው። (ምሳሌ 21:5) ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ፈቃድ እንዲሰጣችሁ አሠሪያችሁን መጠየቅን፣ የትዳር ጓደኛችሁ የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ ወይም ካልሆነች ስለ ሁኔታው መወያየትን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ በሦስቱም ቀን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መርዳትን ይጨምራል። እነዚህን አስፈላጊ ጉዳዮች ለመፈጸም ዛሬ ነገ እያላችሁ አታመንቱ። ከዚህ ይልቅ ‘እርሱ እንደሚያከናውንላችሁ’ በመተማመን ጉዳዩን አስመልክታችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ።—መዝ. 37:5
3. የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞችና እህቶች እንዴት መርዳት ይቻላል?
3 ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው፦ ምሳሌ 3:27 “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ” ይላል። ከስብሰባው ጋር በተያያዘ ለሌሎች መልካም ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች፣ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዲሁም ሌሎች ወንድሞች ከመጓጓዣ ወይም ከማረፊያ ቦታ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ተግባራዊ ድጋፎች ያስፈልጓቸው ይሆናል። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች በመርዳቱ በኩል ቀዳሚነቱን ሊወስዱ የሚገባቸው የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ናቸው። (1 ጢሞ. 5:4) ይሁንና እነርሱ እንዲህ ማድረግ የማይችሉ ከሆኑ የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይችላሉ። (ገላ. 6:10) ችግር ያለባቸው የሚሞሉት መኝታ መጠየቂያ ቅጽ ማግኘት የሚችሉት ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ጉባኤው ማረፊያ ሊያዘጋጁላቸው ያልቻሉ አስፋፊዎች ብቻ ናቸው። የዚህ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት የታረመ ጠባይ የሚያሳዩ ልጆች ያሏቸውና በመንፈሳዊ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ብቻ ናቸው። በቂ መቀመጫ ወንበሮች፣ ጽሑፎች፣ ማረፊያዎችና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሟሉ ለማድረግ የአውራጃ ስብሰባውን ከጉባኤያችሁ ጋር መካፈላችሁ መልካም ይሆናል።
4. የአውራጃ ስብሰባው ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
4 ፈቃደኛ ሠራተኞች:- በስብሰባው ላይ ተገኝተው ከሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብና ገንቢ ከሆነው የወዳጅነት ስሜት የሚቋደሱ ሁሉ እጅግ እንደሚደሰቱ አያጠራጥርም። በተለይም ደግሞ ስብሰባው የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ በሚያደርጉ አንዳንድ ሥራዎች ላይ በፈቃደኝነት ስንካፈል ደስታችን ይበልጥ ይጨምራል። (ሥራ 20:35) በቅርቡ የአካባቢው የአውራጃ ስብሰባ ኮሚቴ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ግብዣ ያቀርባል። አንተስ ራስህን በፈቃደኝነት ታቀርባለህ?—መዝ. 110:3
5. ዓመታዊውን የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም እንድታደንቅ የሚያደርግህ ምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔህስ ምን መሆን አለበት?
5 በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘ የአምስት ዓመት ልጅ “የአውራጃ ስብሰባ በይሖዋ አምልኮ ውስጥ እጅግ የምወደው ነገር ነው” ብሏል። ይህ ከልብ የመነጨ አስተያየት በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ መገኘታችን ምን ያህል አስደሳች ሊሆንልን እንደሚችል እንድንገነዘብ ይረዳናል። በእርግጥም መዝሙራዊው እንደዘመረው ሁሉ “በሌላ ስፍራ ሺህ ቀን ከመኖር፣ በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል።” (መዝ. 84:10) ዳዊት ‘በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ለመኖርና በመቅደሱ ሆኖ ለማሰላሰል’ የነበረውን ፍላጎት በመዝሙር ገልጿል። (መዝ. 27:4) ዳዊት ከይሖዋ አምላኪዎች መካከል መገኘቱ እጅግ አስደስቶታል። እኛም ዳዊት ለእውነተኛው አምልኮ የነበረውን ከፍተኛ አድናቆት በመኮረጅ “መዳናችን ቀርቧል” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሁሉንም ቀን እንገኝ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
የስብሰባው ሰዓት
ዓርብ እና ቅዳሜ
ከ3:30 እስከ 11:15
እሁድ
ከ3:30 እስከ 10:15