ጥያቄ በመጠየቅና በማዳመጥ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ብዙ ሰዎች ሐሳባቸውን መግለጽ ቢያስደስታቸውም እንዲሰበኩ ወይም የምርመራ ዓይነት ጥያቄ እንዲጠየቁ ግን አይፈልጉም። በዚህም ምክንያት ክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የሰዎችን አመለካከት ለማወቅ በዘዴ ጥያቄ የማቅረብ ችሎታ ማዳበር ያስፈልገናል።—ምሳሌ 20:5
2 ጥያቄዎቻችን ሰዎች በተነሳው ነጥብ ላይ እንዲያስቡበት የሚጋብዙ እንጂ የሚያሸማቅቁ መሆን የለባቸውም። አንድ ወንድም ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግልበት ጊዜ እንዲህ በማለት ይጠይቃል:- “ሰዎች አንዳቸው ለሌላው አክብሮትና አሳቢነት የሚያሳዩበት ጊዜ ይመጣል ብለው አስበው ያውቃሉ?” ከዚያ በኋላ በመልሱ ላይ በመመርኮዝ “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዲኖር ምን የሚያስፈልግ ይመስልዎታል?” ወይም “እንዲህ እንዲሰማዎት ያደረገው ምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃል። ሌላ ወንድም ደግሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ልጆች ላሏቸው ሰዎች ሲመሠክር “ወላጅ በመሆንዎ ይበልጥ የሚያስደስትዎት ነገር ምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃቸዋል። አክሎም “ከሁሉ በላይ የሚያሳስብዎትስ ነገር ምንድን ነው?” ይላቸዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ሰዎች ሳይሸማቀቁ የራሳቸውን አመለካከት ለመግለጽ የሚያስችሏቸው እንደሆኑ ልብ በል። የሰዎች ሁኔታ ስለሚለያይ በጥያቄያችን ላይ የምናነሳውን ርዕስም ሆነ የምንጠይቅበትን መንገድ በመለዋወጥ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንደሚስማማ አድርገን ማቅረብ ይኖርብናል።
3 ሰዎች በልባቸው ውስጥ ያለውን እንዲናገሩ መርዳት:- ሰዎች ሐሳባቸውን ለማካፈል ፈቃደኞች ከሆኑ ንግግራቸውን ሳታቋርጥ በትዕግሥት አዳምጣቸው። (ያዕ. 1:19) ለሰጡት ሐሳብ በደግነት አመስግናቸው። (ቈላ. 4:6) “ጥሩ ሐሳብ ነው። ይህንን ሐሳብ ስላካፈሉኝ አመሰግንዎታለሁ” ማለት ትችላለህ። እንድታመሰግናቸው የሚያደርግ ነገር ካገኘህ ከልብህ አመስግናቸው። ምን እንደሚያስቡና እንደዚህ የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በደግነት ተጨማሪ ጥያቄዎችን ጠይቃቸው። የምትስማሙባቸውን የጋራ ነጥቦች ፈልግ። “ይህ መፍትሔ ይሆናል ብለው አስበው ያውቃሉ?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ትኩረታቸውን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ማዞር ትችላለህ። ድርቅ ማለት ወይም መከራከር አይኖርብህም።—2 ጢሞ. 2:24, 25
4 በአብዛኛው ሌሎች ለጥያቄዎቻችን የሚሰጡት መልስ እኛ በምናዳምጥበት መንገድ ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። ሰዎች በጥሞና የምናዳምጣቸው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይችላሉ። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የተመለከተውን ሲናገር “ሰዎችን በትዕግሥት ለማዳመጥ የምታሳየው የፈቃደኝነት መንፈስ፣ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ከመሆኑም በላይ ፍቅራዊ አሳቢነት የምናሳይበት መንገድ ነው” ብሏል። ሌሎችን ማዳመጥ እንዳከበርናቸው እንዲሰማቸው ሊያደርግ እንዲሁም ልናካፍላቸው የምንፈልገውን ምሥራች ለማዳመጥ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ሮሜ 12:10