የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ—መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የምንጠቀምበት ዋነኛ ጽሑፍ
1 “አምላካዊ ታዛዥነት” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ መውጣቱ ሲነገረን ደስታችን ወደር አልነበረውም! ተሰብሳቢዎች ቅዳሜ ዕለት ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ የግል ቅጂያቸውን በማግኘታቸውም ተደስተዋል። ይህን አዲስ ጽሑፍ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን? ይህ ጽሑፍ በዋነኝነት የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ነው። ምንም እንኳ አዲሱ መጽሐፍ ለሰዎች የሚበረከተው መጋቢት ወር ላይ ቢሆንም አስፋፊዎች በእጃቸው ከደረሰበት ዕለት አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርም ሆነ ለመምራት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
2 በማጥናት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች:- በአሁኑ ወቅት በእውቀት መጽሐፍም ይሁን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በሚለው ብሮሹር ጥናት በመምራት ላይ የሚገኙ አስፋፊዎች አዲሱን መጽሐፍ መቼ ማጥናት መጀመር እንዳለባቸው ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ጥናቱ የተጀመረው በቅርቡ ከሆነ አዲሱን መጽሐፍ ከምዕራፍ አንድ በቀጥታ መጀመር ትችላላችሁ። እውቀት መጽሐፍ ስታስጠኑ ለብዙ ጊዜያት ከቆያችሁ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ያለውን ምዕራፍ መርጣችሁ ጥናቱን መቀጠል ትችሉ ይሆናል። እውቀት መጽሐፍ ማገባደጃ ላይ ከሆናችሁ ደግሞ ይህንኑ ጽሑፍ አጥንታችሁ መጨረስ ትችላላችሁ።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ሊጠቀሙ ይችላሉ ብለን የምናስባቸው በርካታ ሰዎች እንደሚኖሩ እሙን ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ በሚያብራራው በዚህ መጽሐፍ ጥናት እንዲጀምሩ ለምን አትጋብዛቸውም? ለምሳሌ ያህል፣ እውቀት መጽሐፍን ወይም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ያጠኑ ቢሆንም እንኳ ራሳቸውን መወሰንና መጠመቅ ደረጃ ላይ ያልደረሱ ካሉ ምናልባት በአዲሱ መጽሐፍ ጥናታቸውን መቀጠል ይፈልጉ ይሆናል። ወላጆች ትክክለኛው የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ልጆቻቸውን ለማስተማር ይህን ጽሑፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።—ቈላ. 1:9, 10
4 ሁለተኛ መጽሐፍ ማጥናት:- ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚለውን መጽሐፍ አጥንቶ የሚጨርስ ሰው ሁለተኛ መጽሐፍ እንዲያጠና የተደረገ ዝግጅት ይኖራል? አዎን አለ። አዝጋሚ ቢሆንም እንኳ ጥናቱ እድገት የሚያደርግ ከሆነና ለተማራቸው ነገሮች አድናቆት ካለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ በተባለው መጽሐፍ መቀጠል ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ እንድንፈጽም የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ እንደሚሆን እንተማመናለን።—ማቴ. 28:19, 20