ከይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
“ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” ጳውሎስ ለጉባኤዎች በጻፋቸው በርካታ ደብዳቤዎች ላይ ይህን ሰላምታ ተጠቅሟል። እኛም ስለ እናንተ ያለንን ምኞት የሚገልጹልን ተስማሚ ቃላት ሆነው አግኝተናቸዋል።—ኤፌ. 1:2
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከይሖዋ ላገኘነው ጸጋ ወይም ይገባናል ለማንለው ደግነቱ ልባዊ አድናቆት አለን! ቤዛው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን አስገኝቶልናል። የቱንም ያህል በትጋት መጽሐፍ ቅዱስን ብናጠና፣ ምሥራቹን ብንሰብክ አሊያም ሌሎች መልካም ተግባራትን ብናከናውን እንዲህ ያለውን መብት በራሳችን ጥረት ልናገኘው አንችልም። የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል። እንዲሁም የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት አጋጣሚ ከፊታችን ተዘርግቶልናል፤ ይሁንና ይህም ቢሆን የድካማችን ዋጋ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያገኘነው የይሖዋ የጸጋ ስጦታ ነው።—ሮሜ 11:6
ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንደሚከተለው ሲል ጽፎላቸው ነበር:- “የተቀበላችሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን። እርሱ፣ ‘በትክክለኛው ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ’ ይላልና። እነሆ፤ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳንም ቀን አሁን ነው።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት የነበረው ጊዜ ለመዳን የሚያስችል “ትክክለኛው ሰዓት” ነበር። በጊዜው ይሖዋን የሚወድዱ ልበ ቅን ሰዎች መንፈሳዊ ጥበቃ አግኝተዋል። ይህ መንፈሳዊ ጥበቃ ኢየሩሳሌም በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከመጥፋቷ ቀደም ብለው ከተማይቱን ለቀው ለወጡት ታማኝ ሰዎች ከጥፋቱ የመትረፍ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።—2 ቆሮ. 6:1, 2
በተመሳሳይም፣ አሁን የምንኖረው ‘በትክክለኛው ሰዓትና’ ‘በመዳን ቀን’ ውስጥ ነው። ይሖዋ አገልጋዮቹ አድርጎ የተቀበላቸውና መንፈሳዊ ጥበቃ ያገኙ ሰዎች በቅርብ ከሚመጣው “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን” የመትረፍ ተስፋ አላቸው።—ሶፎ. 1:14
የይሖዋ ቀን መቅረቡ ከባድ ኃላፊነት ጥሎብናል። ቀኑን አስመልክቶ ሰዎችን ማስጠንቀቅ እንዲሁም ከጸጋው ወይም ይገባናል ከማንለው የይሖዋ ደግነት ተጠቃሚ ሆነው እነርሱም ከጥፋቱ ይተርፉ ዘንድ ልበ ቅኖችን መርዳት ይኖርብናል። ጳውሎስ ይህ ኃላፊነት እንዳለበት በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም “ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ” ሲል ጽፏል። ምን ይሰማው እንደነበረም ሲገልጽ “ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ፣ ዕዳ አለብኝ፤ . . . ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው” ብሏል።—1 ቆሮ. 9:16፤ ሮሜ 1:14, 15
ሰዎችን የማስጠንቀቁን ሥራ ችላ ብንል ይሖዋ በኃላፊነት ይጠይቀናል። ይሖዋ ለነቢዩ ሕዝቅኤል ምን እንዳለው መዘንጋት አይኖርብንም:- “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ ቃሌን ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው። እኔ ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።”—ሕዝ. 3:17, 18
እነዚህ የመጨረሻ ቀናት አስጨናቂ ናቸው። የቤተሰብ ጉዳዮችን፣ ሥራን፣ የጉባኤ እንቅስቃሴን እንዲሁም የስብከቱን ሥራ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማካሄድ ቀላል አይደለም። ከዚህም በላይ ብዙዎቻችሁ ካለባችሁ ሕመም፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ የዕድሜ መግፋት እንዲሁም ከሚገጥማችሁ ተቃውሞ ጋር መታገል ግድ ሆኖባችኋል። አብዛኞቻችሁ ‘ሸክሙ ከብዶባችኋል።’ እኛም ኢየሱስ “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” ብሎ የተናገረውን የመሰለ የአሳቢነት ስሜት እንዳለን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። (ማቴ. 11:28) ያሉባችሁ ችግሮች ቀላልም ይሁኑ ከባድ ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኙትን ሁሉ እጅግ እናመሰግናችኋለን።
በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በቅንዓት በመካፈላችሁ እንዲሁም ይሖዋ ይህን ጥረት ስለባረከው በየሳምንቱ በአማካይ በዓለም ዙሪያ 4,762 የሚሆኑ ሰዎች ይጠመቃሉ። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 1,375 የሚሆኑ አዳዲስ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። በአሁኑ ጊዜ በ120 ቋንቋዎች የታተመውና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው አዲስ መጽሐፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገባናል የማንለውን የይሖዋ ደግነት እንዲቀምሱ እንዲሁም በዚህ ‘የመዳን ቀን’ ይሖዋ የሚሰጠውን ሰላም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ይህ እንዲሆንም ዘወትር እንጸልያለን።
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል እንደሚወዳችሁና ስለ እናንተም እንደሚጸልይ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። እናንተም ለእኛ ስለምትጸልዩልን እናመሰግናችኋለን።
ወንድሞቻችሁ፣
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል