ይሖዋን በከፍተኛ ጉጉት ተጠባበቁ
1. የአውራጃ ስብሰባው ጭብጥ ምንድን ነው? ወቅታዊ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?
1 ኢሳይያስ፣ “እግዚአብሔር የፍትሕ [“የፍርድ፣” የ1954 ትርጉም] አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት የተባረኩ ናቸው” በማለት ጽፏል። (ኢሳ. 30:18ለ) ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የቅጣት ፍርድ እንዳስፈጸመና ታማኝ አገልጋዮቹን እንዳዳነ የሚናገሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይገኛሉ። በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ አምላኪዎች ከእነዚህ ዘገባዎች የሚያገኙት ትምህርት ምንድን ነው? ‘ታላቁንና የሚያስፈራውን የይሖዋ ቀን’ ዝግጁ ሆነን ለመጠባበቅ አሁን ምን ማድረግ እንችላለን? (ኢዩ. 2:31, 32) በቅርቡ የምናደርገው “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በማሰላሰል ራሳችንን እንድንመረምር ያነሳሳናል። እንዲሁም ይሖዋን በመተማመን ወይም በከፍተኛ ጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል።
2. ለአውራጃ ስብሰባችን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
2 በሦስቱም የአውራጃ ስብሰባ ቀናት ላይ ተገኝተህ ትምህርት ለመቅሰም ተዘጋጅተሃል? ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪህን ቀርበህ በስብሰባው ላይ ለመገኘት የሚያስችልህን እረፍት እንዲሰጥህ ጠይቀሃል? ቀደም ብለህ ሳትጠይቅ እረፍት ማግኘት እንደምትችል አይሰማህ። በጉዳዩ ላይ ከጸለይክ በኋላ ለአሠሪህ ጥያቄህን አቅርብ። (ነህ. 2:4, 5) በተመሳሳይም ለመጓጓዣ፣ ለማረፊያ ቦታና ለሌሎች ነገሮች የሚያስፈልገውን ዝግጅት ለማጠናቀቅ ዛሬ ነገ ማለት አይኖርብንም። እንዲህ ያለው ቅድመ ዝግጅት ለይሖዋ መንፈሳዊ ማዕድ ያለንን ጥልቅ አድናቆት የሚያሳይ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች በአውራጃ ስብሰባው ለመገኘት ዝግጅት በማድረግ ረገድ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን በተለይም በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን ለመርዳት ንቁ መሆን ይገባቸዋል።—ገላ. 6:10
3. የይሖዋ ሕዝቦች የአውራጃ ስብሰባቸውን በሚያደርጉበት አካባቢ የትኞቹን ባሕርያት ማሳየት ይገባቸዋል?
3 መልካም ባሕርይ አምላክን ያስከብራል:- በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በብዛት ስንሰበሰብ የምናሳየው መልካም ጠባይ በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች ምሥክርነት ይሰጣል። ይህ ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል? የአውራጃ ስብሰባው በሚካሄድበት አካባቢ ወደሚገኙ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና ሌሎች የንግድ ቤቶች ስንሄድ ለምናገኛቸው ሰዎች እንደ ትዕግሥት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛትና ምክንያታዊነት ያሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ልናሳያቸው ይገባል። (ገላ. 5:22, 23፤ ፊልጵ. 4:5 NW) ሁላችንም ‘ተገቢ ያልሆነ ነገር የማያደርገውን፣ ራስ ወዳድ ያልሆነውንና የማይበሳጨውን’ ፍቅርን ማንጸባረቅ ይኖርብናል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ እንኳ “ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር” ማድረግ እንፈልጋለን።—1 ቆሮ. 10:31፤ 13:5
4. ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን የሚያስከብር ጠባይ እንዲኖራቸው ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
4 ወጣቶች የሚያሳዩት መልካም ጠባይ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ሥልጠና እንደሰጡና ተገቢውን ቁጥጥር እንደሚያደርጉ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ያለምንም ቁጥጥር እንደልባቸው እንዲሆኑ መተዋቸው ተገቢ አይሆንም። ልጆች ሁልጊዜም ቢሆን ተገቢ ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 29:15) በመልካም ጠባያቸው ለይሖዋ ክብር እንዲያመጡና ልቡንም ደስ እንዲያሰኙት እንመኛለን!—ምሳሌ 27:11
5. በአለባበሳችንና በአበጣጠራችን ይሖዋን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
5 ጨዋነት የሚንጸባረቅበት አለባበስና አበጣጠር:- ቅጥ ያጣ፣ ጨዋነት የጎደለው ወይም ግዴለሽነት የተንጸባረቀበት ዘመን አመጣሽ አለባበስና አበጣጠር ባለመከተል እያንዳንዳችን የአውራጃ ስብሰባው ክብር የተላበሰ እንዲሆን የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን። ይህ ደግሞ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ ስንጓዝም ሆነ ከዚያ ስንመለስ፣ የመሰብሰቢያውን ቦታ በማዘጋጀቱ ሥራ ላይ ስንካፈል እንዲሁም በስብሰባው ላይ ስንገኝ የሚኖረንን አለባበስ ይጨምራል። የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከምንም በላይ የሚያሳስበን የራሳችን ምርጫና ፍላጎት ሳይሆን የይሖዋ ስም መከበር ነው። የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸው አባላት አለባበስና አበጣጠር በማንኛውም ጊዜ ጨዋነትና ጤናማ አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት መሆኑን የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው።—1 ጢሞ. 2:9
6. ስብሰባው ከሚደረግበት ሰዓት ውጪም አለባበሳችን የሚያስከብር መሆኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ስብሰባው ከሚደረግበት ሰዓት ውጪ ወደ ሆቴሎች፣ ሱቆች እንዲሁም ምግብ ቤቶች ስንሄድ አለባበሳችን የሚያስከብር መሆኑ የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ምሳችንን ውጪ የምንበላ ከሆነ ለስብሰባ የለበስነውን ልብስ ባንቀይር ጥሩ ነው። የአውራጃ ስብሰባችንን ባጅ ካርድ ማድረጋችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ይከፍትልናል።—2 ቆሮ. 6:3, 4
7. የአውራጃ ስብሰባው ሥርዓታማና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? (“የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች” የሚለውን ተመልከት።)
7 ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 30:18ሀ) ይሖዋ ላሳየን ምሕረትና ይገባናል ለማንለው ደግነቱ ያለን አድናቆት በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አብረን በምንሰበሰብበት ጊዜ በጠባያችንም ሆነ በአለባበሳችን እንድናከብረው ያነሳሳናል። “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ አምላካችንን የሚያስከብር እንዲሆንና እርሱን በከፍተኛ ጉጉት እንድንጠባበቅ እንዲረዳን እንመኛለን!
[ገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአውራጃ ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
◼ ሰዓት:- ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:30 ላይ ይጀምራል። ከጠዋቱ 2:00 በሮች ይከፈታሉ። እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሊቀ መንበሩ የመክፈቻ ሙዚቃው እየተሰማ እያለ መድረክ ላይ በተዘጋጀለት ወንበር ላይ ይቀመጣል። በዚህ ወቅት ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል። ይህም ስብሰባውን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመጀመር ያስችላል። ፕሮግራሙ ዓርብ 11:15፣ ቅዳሜ 11:05 እንዲሁም እሁድ 10:10 ላይ ይደመደማል።
◼ መቀመጫ መያዝ:- መቀመጫ መያዝ የሚቻለው አብረዋችሁ ለሚኖሩና ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ።
◼ ምሳ:- በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ የስብሰባውን ቦታ ትታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። አስፈላጊ ከሆነ በመቀመጫችሁ ሥር ሊቀመጥ የሚችል መጠነኛ የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
◼ መዋጮዎች:- የአውራጃ ስብሰባዎችን ማደራጀት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ አድናቆታችንን ማሳየት እንችላለን። በስብሰባው ላይ መዋጮ የሚደረጉ ቼኮች ለ “የይሖዋ ምሥክሮች” [“Yeyihowa Misikiroch”] የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት።
◼ አደጋዎችና ድንገተኛ ሕመም:- አንድ ሰው በስብሰባው ቦታ ላይ ድንገተኛ ሕመም ካጋጠመው የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ ክፍል የሚገኝበትን ቦታ እንዲጠቁማችሁ በቅርብ ያለውን አስተናጋጅ አነጋግሩ።
◼ የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች:- የትኛውንም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር ማገናኘት አይፈቀድም። እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ሌሎች ስብሰባውን እንዳይከታተሉ የማያደናቅፍ መሆን ይገባዋል።
◼ ፎቶግራፍ ማንሳት:- ስብሰባው እየተካሄደ እያለ ፎቶግራፍ ማንሳት ከፈለጋችሁ እባካችሁ ፍላሽ አትጠቀሙ።
◼ ሞባይል ስልኮች:- በሞባይል ስልኮች ምክንያት የሌሎች ትኩረት እንዳይከፋፈል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
◼ ቅጾች:- እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ስላሳየ ሰው መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ይህ ቅጽ በአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል ይገኛል። ግለሰቡን ተከታትሎ መርዳት እንዲቻል ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለአውራጃ ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።—የየካቲት 2005 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6ን ተመልከቱ።