በመንፈሳዊ የምንመገብበትና የምንደሰትበት ዝግጅት
1. ይሖዋ የአገልጋዮቹን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያሟላው እንዴት ነው?
1 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የአገልጋዮቹን መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟላል። ዓለም በመንፈሳዊ በተራበበት በዚህ ጊዜ እኛ የተትረፈረፈ ምግብ ይቀርብልናል። (ኢሳ. 65:13) ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ከሚጠቀምባቸው ዝግጅቶች መካከል ዓመታዊ የአውራጃ ስብሰባዎች ይገኙበታል። “በአምላክ መንፈስ መመራት” የሚል ርዕስ ባለው በመጪው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሦስቱንም ቀናት ጠዋትም ሆነ ከሰዓት ለመገኘት ዝግጅት እያደረግክ ነው? በጣም ጣፋጭና ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ተዘጋጅቶልናል።
2. ለስብሰባው አስቀድሞ እቅድ ማውጣት ምን ምን ነገሮችን ይጨምራል?
2 አስቀድመህ እቅድ አውጣ:- “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል።” (ምሳሌ 21:5) በመሆኑም በስብሰባው ላይ ሦስቱንም ቀናት ለመገኘት ያወጣኸውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ፈቃድ መውሰድ ይኖርብህ ይሆን? ከሆነ አሠሪህን ለማነጋገር ዛሬ ነገ አትበል። ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ውስጥ ማረፊያ የሚያስፈልግህ ከሆነ ከአሁኑ ዝግጅት አድርገሃል? በተጨማሪም ምሳህን ስብሰባው በሚደረግበት ቦታ ላይ ከወንድሞች ጋር መመገብ እንድትችል ከወዲሁ እቅድ ብታወጣ ጥሩ ይሆናል። የምትቀመጥበትን ቦታ ማግኘት እንዲሁም በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ላይ መካፈል እንድትችል ስብሰባዎቹ በሚደረግባቸው ቀናት ቀደም ብለህ ለመድረስ ዝግጅት አድርግ።
3. ምን ዓይነት አለባበስ ሊኖረን ይገባል?
3 የምንለብሳቸው ልብሶች ልከኛና ሥርዓታማ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንፈልጋለን። (1 ጢሞ. 2:9, 10) የአውራጃ ስብሰባዎች ለአካባቢው ኅብረተሰብ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍቱልናል። ስብሰባው በሚካሄድበት ከተማ በምንቆይባቸው ቀናት ክብር በሚያንጸባርቅ መንገድ በመልበስ እንዲሁም ባጃችንን በማድረግ ከማያምኑ ሰዎች ተለይተን ለመታየትና ሌሎች ለእኛ ጥሩ ስሜት እንዲያድርባቸው ለማድረግ መጣር ይኖርብናል።
4. እኛም ሆንን ቤተሰባችን ከፕሮግራሙ ሙሉ ተጠቃሚ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
4 በጥሞና አዳምጡ:- በዚህ መንፈሳዊ ግብዣ ላይ ከሚቀርብልን ምግብ ምንም እንዲያመልጠን እንደማንፈልግ ግልጽ ነው! (ምሳሌ 22:17, 18) ጥቅሶች ሲነበቡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን አውጥተን መከታተላችን እንዲሁም አጭር ማስታወሻ መያዛችን አእምሯችን በትምህርቱ ላይ እንዲያተኩርና ሐሳባችን እንዳይባዝን ይረዳናል። ምሽት ላይ የስብሰባውን ዋና ዋና ነጥቦች አንስተን ከሌሎች ጋር ለመወያየት የያዝነውን ማስታወሻ መጠቀም እንችላለን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንድ ወጣቶች በስብሰባው ወቅት አብረው በመቀመጥ እርስ በርስ እንደሚያወሩ ወይም በሞባይላቸው መልእክት እንደሚለዋወጡ ተስተውሏል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ ልጆች ካሉን ከእኛ ተለይተው ከሌሎች ወጣቶች ጋር እንዲቀመጡ ከመፍቀድ ይልቅ አብረናቸው ተቀምጠን በቤተሰብ ደረጃ ፕሮግራሙን መከታተላችን ጠቃሚ ነው።
5. ከስብሰባው የበለጠ ደስታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
5 ከሌሎች ጋር ተቀራረቡ:- ጣፋጭ ምግብ ይበልጥ የሚጥመው ከሌሎች ጋር ሲመገቡት ነው። (ምሳሌ 15:17) በተመሳሳይም ከወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረባችን ከስብሰባው የበለጠ ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። በመሆኑም ከስብሰባው ሰዓት ውጪ ቅድሚያውን በመውሰድ ከሌሎች ጋር መተዋወቃችንና መጨዋወታችን ምንኛ አስደሳች ይሆናል! (መዝ. 133:1) ሊቀ መንበሩ ሙዚቃው ከመጀመሩ በፊት ቦታ ቦታችንን እንድንይዝ በአክብሮት ይጠይቀናል፤ በዚህ ወቅት ሁላችንም ጭውውታችንን አቋርጠን በመቀመጥ ፕሮግራሙ የሚጀምርበትን ሰዓት መጠባበቅ ይኖርብናል።
6. የአውራጃ ስብሰባው በሚደረግበት ከተማ ላሉ ሰዎች እንዴት መመሥከር እንደምንችል የሚያሳይ በግል ያገኘኸው ተሞክሮ ካለ ተናገር።
6 ለመመሥከር ንቁዎች ሁኑ:- አብዛኛውን ጊዜ የአውራጃ ስብሰባዎች ለሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍቱልናል። ከስብሰባው በኋላ ወደ ምግብ ቤቶች የሚሄዱ ብዙ ወንድሞችና እህቶች በባጃቸው ላይ ያለውን የስብሰባ ጭብጥ በተመለከተ ከአስተናጋጆችና ከሌሎች ሰዎች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ይህ ደግሞ ውይይት ለመጀመርና ስለ እውነት ለመመሥከር መንገድ ከፍቷል። ጥያቄ ከጠየቁት ሰዎች አንዳንዶቹ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።
7. በመጪው የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
7 ወንድሞች ስብሰባውን ለማዘጋጀት፣ የመሰብሰቢያውን ቦታ ለማሰናዳት፣ የተለያዩ የአውራጃ ስብሰባ ዲፓርትመንቶችን ለማደራጀትና ንግግሮችን ለመዘጋጀት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዓታትን ያጠፋሉ። አፍቃሪ የሆኑት ወንድሞቻችን ይህን መንፈሳዊ ድግስ ለማዘጋጀት የሚያጠፉት ጉልበት ይሖዋ ለሕዝቡ ከልብ እንደሚያስብ የሚያሳይ ነው። ሁላችንም በቦታው ተገኝተን በሚገባ እንመገብ! በዓለም ላይ ካሉት ሰዎች በተለየ መልኩ እኛ ይህን ማድረጋችን ‘ከልብ በመነጨ ደስታ እንድንዘምር’ ያስችለናል።—ኢሳ. 65:14